ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የየመን ጦርነት፡ አሜሪካ ለሳኡዲ መራሹ የየመን ጦርነት ድጋፍ መስጠት አቆመች
አሜሪካ ለሳኡዲ መራሹ የየመን ጦርነት ድጋፍ መስጠት አቆመች።
ከ110 ሺህ ሕዝብ በላይ ሕይወቱን አጥቶበታል ለሚባለውና 6 ዓመታት ለዘለቀው የየመን ጦርነት አሜሪካ ከዚህ በኋላ ድጋፍ እንደማትሰጥ ይፋ አደረገች።
አሜሪካ በዚህ የሳኡዲ መራሽ የየመን ጦርነት ለሳኡዲ አረቢያና ለተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የመሣሪያ ሽያጭና ሌሎች ድጋፎች ታደርግ ነበር።
'የየመን ጦርነት አሁን ማብቃት አለበት' ብለዋል አዲሱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለመጀመርያ ጊዜ በውጭ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ንግግር።
ከባይደን በፊት የነበሩት ሁለቱ የአሜሪካ አስተዳደሮች ለየመን ጦርነት ተዋጊዎች መልከ ብዙ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር።
ሳኡዲ መራሹ ኃይል በየመን የሑቲ አማጺዎችን ለማንበርከክ ዘመናዊ መሣሪያዎችን ሲጠቀም ቢቆይም አልተሳካለትም።
ይልቅም ጦርነቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የመናውያንን ለረሀብና እርዛት ያጋለጠ ሆኗል።
ይህ ጦርነት የተቀሰቀሰው እንደ አውሮጳውያኑ በ2014 የነበረ ሲሆን ያን ጊዜ ተዳክሞ የነበረው ማዕከላዊው መንግሥት በሑቲ ሚሊሻዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሞበት ነበር።
ከአንድ ዓመት በኋላ በርካታ የውጭ ኃይሎች እጃቸውን ማስገባታቸውን ተከትሎ ይህ የውስጥ ችግር ወደለየለት ውስብስብ ጦርነት አድጓል።በዚህ ጦርነት ሳኡዲ ከሌሎች 8 የአረብ አገራት ጋር በመተጋገዝ፣ እንዲሁም ከታላቋ ብሪታኒያ፣ ከአሜሪካና ከፈረንሳይ ልዩ ድጋፍ በማግኘት በየመን ሑቲዎች ላይ ቦምብ ስታዘንብ ኖራለች።
አሜሪካ በተለይም በትራምፕ አስተዳደር ከባባድ የጦር መሣሪያዎችን ለሳኡዲ መንግሥት ታቀርብ ነበር።
አሁን ባይደን በዚህ ጦርነት አሜሪካ የተለየ ፖሊሲ እንደምትከተል ይፋ ያደረጉ ሲሆን ለሳኡዲ መራሹ ሠራዊትም ድጋፍ እንደማትሰጥ ይፋ አድርጋለች።
ባይደን ከዚህ ሌላ በውጭ ፖሊሲዎች ላይ አዳዲስ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል። ከነዚህም መካከል አሜሪካ ከእንግዲህ በምትቀበላቸው ስደተኞች ቁጥር ጭማሪ እንደምታደርግ፣ ወታደሮቿን ከጀርመን የማስወጣቱን ሐሳብ እርግፍ አድርጋ እንደምትተው አስታውቀዋል።
አሜሪካ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት ወዲህ በጀርመን ወታደሮችን እንዳሰፈረች ቆይታለች።
ጆ ባይደን ባደረጉት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ያተኮረ ንግግር ከአንድ ወር በፊት ሥልጣን ከለቀቁት የቀድሞት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፖሊሲዎችን አንድ በአንድ እያጠፏቸው እንደሆነ አሳይተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው በዓለም ላይ አሁን እንደ የመን የሰብአዊ ቀውስ ያለበት አገር የለም። የመን የሕዝቧ 80 ከመቶ አንዳች አይነት የምግብ ወይም የመጠለያ ድጋፍን የሚሻ ነው።