አሜሪካ፡የመን ውስጥ የታገቱት አሜሪካውያን በእስረኛ ልውውጥ ተለቀቁ

ታትሟል

የመን ውስጥ በሁቲ አማጺያን ታግተው የነበሩ የሁለት አሜሪካውያን በእስረኞች ልውውጥ አማካይነት መለቀቃቸው ተሰምቷል።

ለሶስት ዓመታት ታግታ የቆየችውና የሰብአዊ እርዳት ስራ ተሰማርታ የነበረችው ሳንድራ ሎሊ እና ለአንድ ዓመት የታገተው በንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶ የነበረው ማይክል ጊዳዳ የተለቀቁት ትናንት እንደሆነ የአሜሪካ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ሌላኛው ታግቶ የነበረው ሶስተኛው ግለሰብ ቢላል ፋቲን አፅምም እንዲመለስ ተደርጓል ተብሏል።

የእስረኞች ልውውጡ የተከናወነው የሁቲ አማጺያን ከ200 በላይ የሚሆኑ የየመን ዜጋዎችን ከኦማን መቀበላቸውን ካስታወቁ በኋላ ነው። ሰዎቹ ህክምና ከተደረገላቸው በኋላ እዛው እንዲቆዩ ተገድደውም ነበር።

በርካታ ዓለም ዓቀፍ ተቋማትና አገራት በቅርበት ሲከታተሉትና በጉጉገት ሲጠባበቁት የነበረው ይህ የእስረኞች ልውውጥ ሐሙስ ዕለት እንደሚከናወን ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን በሳዑዲ የሚደገፈው የየመን መንግስትና የሁቲ አማጺያን መካከል ለጊዜውም ቢሆን መግባባትን ፈጥሯል።

የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ላይም የሁለቱ ዜጎች በሰላም መለቀቅ ትልቅና የሚያስደስት ዜና መሆኑን በመግለጽ ሕይወቱ ላለፈችው ሶስተኛ ግለሰብ ቤተሰቦች ደግሞ መጽናናትን ተመኝቷል።

የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ሮበርት ኦብራያን በበኩላቸው የኦማን ንጉስ ሱልጣን ሃይታም ቢን ታሪቅ እና የሳኡዲውን ንጉስ ሳልማንን ላደረጉት ትብብር በማመስገን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የሁቲ አማጺያን ቃለ አቀባይ የሆኑት ሞሀመድ አብዱሰላም በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ወደ ኦማን ሲሄዱ መንገድ ላይ የቀሩ አልያም ህክምና ለማግኘት ወደ ኦማኗ ዋና ከተማ ማስካት የተጓዙ 240 የሚሆኑ የመናውያን መመሳቸውን ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ አክለውም ኦማን ላደረገችው የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ያመሰገኑ ሲሆን ስለተለቀቁት አሜሪካውያን ታጋቾች ግን ምንም ያሉት ነገር የለም።

የአሜሪካው ዎልስትሪት ጆርናል ሲሆን የአሜሪካውያኑን መለቀቅ ዜና ያበሰረው ድርድሩ በፍጥነት የተከናወነው አንደኛ ታጋች ጤናዋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ እንደሆን ዘግቧል።

አክሎም ስምምነቱ አሜሪካ ለየመን የጤና ድጋፍ እንድታደርግም ተካትቶበታል ብሏል።

በአውሮፓውያኑ 2015 አማጺያን የአገሪቱን ምዕራባዊ ክፍል በብዛት መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የመን በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ የቆየች ሲሆን ፕሬዝዳንት አብደራቡህ ማንሱር ሃዲ አገር ለቀው ተሰድደዋል።

የእርስ በርስ ጦርነቱም በዓለም ላይ ከፍተኛው የተባለውን የሰብአዊ ቀውስ አስከትሏል። ጦርነቱን ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቀላሉ መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች ሕይወታቸው አልፏል።