ኮሮናቫይረስ፡ እስራኤል 5ሺ የኮቪድ ክትባት ጠብታዎችን ፍልስጤማዊያን ልትሰጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
9 ሚሊዮን ሕዝቧን በሙሉ ለመከተብ በከፍተኛ ዘመቻ ላይ የሆነችው እስራኤል 5ሺ ጠብታ ክትባቶችን ለፍልስጤማዊያን አበረክታለሁ ብላለች።
ሆኖም እነዚህ ክትባቶች የሚሰጡት በፍልስጤም የጤና መኮንን ለሆኑ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ነው።
እስራኤል በአሁን ሰዓት በጣም የተቀላጠፈ የክትባት ዘመቻ በማካሄድ ላይ ካሉ የዓለም አገራት ቁንጮዋ ናት።
ሆኖም በዌስት ባንክና ጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማዊያን ይህ ወግ አልደረሳቸውም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስራኤል በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚኖሩ ፍልስጤሞችን የመከተብ ግዴታ አለባት ሲል አሳስቧል።
ሆኖም እስራኤል በመጀመርያ ይህ ግዴታ የለብኝም፤ በሁለተኛ ደረጃ ከፍልስጤም አስተዳደርም ቢሆን ጥያቄው አልቀረበልኝም ብላለች።
እስራኤል 640ሺህ ዜጎች በተህዋሲው ተይዘውባት 5ሺ የሚጠጉት ሞተውባታል።
ይበልጥ የተጠቁት ደግሞ በዌስት ባንክና በጋዛ 160ሺ ፍልስጤማዊያን በተህዋሲው እንደተያዙና ወደ 2ሺ የሚጠጉት እንደሞቱ ጥናቶች ያሳያሉ።
እስራኤል ክትባት እያቀረበላት ካለው ፋይዘር ጋር ያላት አንዱ ስምምነት በዜጎች ጤና ላይ መረጃን ለመድኃኒት አምራቹ በየጊዜው ማቅረብ ነው።
እስራኤል እስከአሁን የሕዝቧን 20 እጅ የኮቪድ ክትባት ከትባለች።
ይህም በድምሩ ወደ 2 ሚሊዮን እየተጠጋ ያለ ቁጥር ነው።
እነዚህ ሕዝቦቿ ታዲያ የፋይዘርን በሳምንታት ልዩነት የሚሰጠውን 2 ጠብታ ክትባት ሙሉ በሙሉ ያገኙ ዜጎች ናቸው።
ከነዚህ ሌላ ደግሞ 3 ሚሊዮን ዜጎቿ የመጀመርያውን ዙር ጠብታ ማግኘት ችለዋል።
አገሪቱ በክትባት ደረጃ ብዙ ርቀት ብትሄድም የእንቅስቃሴ ገደቦች አሁንም እንዳሉ ነው ያሉት።
የእሰራኤል መከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ቤኒ ጋንዝ ቢሮ እንዳረጋገጠው እስራኤል የተወሰኑ ጠብታዎቹን ወደ ፍልሥጤም አስተዳደር ታስተላልፋለች።
ጠብታዎቹን ግን ፍልስጤሞች እሺ ብለው ስለመቀበል አለመቀበላቸው ያሉት ነገር የለም።
በፍልስጤም ከፊል አስተዳደር ሥር የሚገኘው ዌስት ባንክም ሆነ በሐማስ አስተዳደር ሥር ያለው ጋዛ ምንም ዓይነት የክትባት ዘመቻን አልጀመሩም።
የፍልስጤም ባለሥልጣናት ከመድኃኒት አቅራቢዎች ጋር ንግግር መጀመራቸው ይግለጹ እንጂ መቼ ክትባት እንደሚደርስና ለሕዝባቸው በምን መንገድ እንደሚያቀርቡ እስከአሁን ያሉት ነገር የለም።
የፍልስጤም ባለሥልጣናት ተስፋ ያደረጉት የዓለም ጤና ድርጅት የሚደግፈውን ኮቫክስ የተሰኘ ፕሮጀክት ጥላ ሥር መታቀፍና ድጋፍ ማግኘትን ነው።
ይህ ፕሮጀክት ድህ አገራት ክትባት እንዲያገኙ የሚያግዝ ነው።
እስከአሁን ጥቂት ሩሲያ ሰራሹ ክትባት ፍልስጤም መድረሱ ቢነገርም ለማን እንደታደለ ግን የሚታወቅ ነገር የለም።
በዌስት ባንክ ወደ 3 ሚሊዮን፣ በጋዛ ደግሞ ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልስጠማዊያን ይኖራሉ።
ለፍልስጤሞች ክትባት የመስጠቱ ኃላፊነት የማን ነው የሚለው ጉዳይ ግን አሁንም እያነጋገረ ነው።
እስራኤል በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ ለመስጠት የኦስሎ ስምምነትን ትጠቅሳለች።
የኦስሎ ስምምነት ዌስት ባንክና ጋዛ የፍልሥጤም አስተዳደር ሙሉ ዘላቂ ሰላም ስምምነት እስኪፈረም በጊዜያዊነት እንዲያስተዳድሩ ስለሚል የጤና ጉዳዮችንም የሚመለከተው ይህን አስተዳደር ነው ስትል ትከራከራለች።
ፍልስጤሞች በበኩላቸው ይህ የኦስሎ ስምምነት አንዳች ወረርሽኝ በመጣ ጊዜ እስራኤል ለጋዛና ዌስት ባንክ ትብብር ትሰጣለች የሚል አንቀጽ እንዳለውም ይጠቅሳሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ባልደረባ ግን በግድ በተያዙ ግዛቶች ሁሉ የጄኔቫ ስምምነት ተግባራዊ እንደሚሆንና ፍልስጤሞችን የመከተቡ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የእስራኤል እንደሆነ ያሰምሩበታል።
የአለም አቀፍ ጉዳዮች አዋቂ የሆኑ ሰዎች በዚህ ረገድ የተለያየ አቋምን ያንጸባርቃሉ።
እስራኤል አሁን የጀመረችው ሰፊ የክትባት ዘመቻ የአረብ እስራኤል ዜጎችን እንዲሁም እስራኤል በጉልበት በያዘቻቸው የምሥራቅ ኢየሩሳሌም አካባቢዎች የሚገኙ ፍልስጠማዊያንን የሚያካትት ነው።












