ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ጋና ውስጥ አዲሱ የኮቪድ-19 መገኘቱ ተገለፀ
የጋናው ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ በአገራቸው አዲሱ የኮሮናቫይርስ ዝርያ መገኘቱን ገለፁ።
ፕሬዝዳንት አኩፎ አዶ አገራቸው አዲሱን የቫይረስ ዝርያ ያገኘችው በዋናው አውሮፕላን ማረፊያ መሆኑን ገልፀዋል።
ፕሬዝዳንቱ በቴሌቪዥን ቀርበው እንዳስታወቁት አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ ያለበት ሰው የተገኘው በአውሮፕላን ማረፊያው በኩል ሊገባ የነበረና ለይቶ ማቆያ እንዲገባ ከተደረገ መንገደኛ ነው።
ስለ መንገደኛው ማንነትም ሆነ ከየትኛዋ አገር ተነስቶ ወደ ጋና እንደመጣ የተባለ ነገር የለም።
የጋና ባለሥልጣናትም አዲሱ ዝርያ ወደ ኅብረተሰቡ ስለመሰራጨቱ ለማወቅ እንደሚጥሩ ተናግረዋል።
ተመራማሪዎች ቫይረሱ ራሱን መለወጡ የተለመደ ነገር ነው ብለዋል።
ጋና በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች እየጨመረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በየቀኑ 200 አዳዲስ ሰዎች በተህዋሲው መያዛቸው እየተመዘገበ ነው።
በአገሪቱ ውስጥ የበሽታው የስርጭቱ መጠን አንደ አዲስ መጨመር ያሳየው በበዓላት ሰሞን በታየው መዘናጋት ነው ተብሏል። ፖሊስ ለኮሮናቫይረስ መከላከል የተቀመጡ ገደቦችን በጥብቅ እንዲያስከብርም ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።
መንግሥት በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን መለየት፣ ምርመራ እና የተያዙ ሰዎች የሚሰጠው ሕክምና ለማጠናከር አቅዷል።
ጋና ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ 57,000 በቫይረሱ መያዛቸውን ሲረጋገጥ ከእነዚህም መካከል 300 ሰዎች ሞተዋል።