ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ ፡ አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ በአሜሪካ በቀጣይ ሳምንታት በከፍተኛ መጠን እንደሚስፋፋ ተነገረ
በከፍተኛ ፍጥነት የሚዛመተውና መጀመሪያ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ መገኘቱ የተገለጸው አዲሱ የኮሮናቫይረስ አይነት በቀጣይ ወራት በአሜሪካ ውስጥ በዋናነት እንደሚስፋፋ የጤና ባለሥልጣናት ተናገሩ።
የአገሪቱ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል እንዳስጠነቀቀው በመጪዎቹ ሳምንታት አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ "በከፍተኛ ፍጥነት" እንደሚጨምር ገልጿል።
እንደተባለው በአሁኑ ጊዜ በመላዋ አሜሪካ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ አሳሳቢ ሆኖ ሳለ አዲሱ የቫይረሱ አይነት ሌላ ስጋትን አስከትሏል።
ይህ ማስጠንቀቂያ የወጣው አርብ ዕለት ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ክትባትን በከፍተኛ መጠን ለማስፋፋት የሚያስችል ግዙፍ ዕቅድን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።
ሥልጣን በያዙ በ100 ቀናት ውስጥ 100 ሚሊዮን ሰዎችን ለመክተብ የያዙትን ዕቅድ ለማሳካት የክትባቱን አቅርቦት ለማጠናከር አስተዳደራቸው ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ተነግሯል።
በፕሬዝዳንቱ ዕቅድ መሠረት ግዙፍ የክትባት መስጫ ማዕከላት ይቋቋማሉ፣ ተጨማሪ የጤና ባለሙያዎች ይቀጠራሉ፣ በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቁ ጥቂት ቁጥር ያላቸው ማኅበረሰቦችን ጨምሮ ክትባቱ ለሁሉም ሰው ይቀርባል ተብሏል።
ይፋዊ መረጃ እንደሚያመለክተው አስካሁን 12.2 ክትባት በአሜሪካ ውስጥ ለሰዎች ተሰጥቷል። ከ30 ሚሊዮን በላይ ክትባቶች በአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ ተሰራጭቷል።
አሜሪካ በዓለም ላይ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ በርካታ ሕዝብ ካለባቸው አገራት ቀዳሚዋ ስትሆን፤ ከ23.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸው ተገልጧል።
ከእነዚህም መካከል 391 ሺህ በላይ የሚሆኑት በበሽታው ምክንያት የሞቱባት ሲሆን በኮቪድ-19 የሞት መጠንም አሜሪካ በዓለም የአምስተኝነት ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በአሁኑ ጊዜ በሽታው ያስከተለው ቀውስ በአሜሪካ ካሉ ግዛቶች ሁሉ በካሊፎርኒያ ውስጥ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱ የተነገረ ሲሆን፤ ከኅዳር ወር ጀምሮ በቫይረሱ ምክንያት የሚሞቶ ሰዎች አሃዝ ከ1000 ሺህ እጥፍ በላይ ጨምሯል።
የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ የዛሬ ዓመት ቻይና ውስጥ መከሰቱ ከተነገረ በኋላ መላውን ዓለም አዳርሶ ከ93 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተመዘገበ ሲሆን የሞቱ ሰዎች አሃዝም ትናንት አርብ ከሁለት ሚሊዮን ማለፉ ተነግሯል።