ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ ፡ ሕንድ በዓለም ትልቁን የኮቪድ-19 ክትባት ዘመቻ ጀመረች
ሕንድ በዓለም ትልቁ የተባለውን የኮሮናቫይረስ የክትባት ዘመቻን ዛሬ [ቅዳሜ] ማካሄድ ጀመረች። በዚህም የንጽህና ሠራተኞች ክትባቱን በማግኘት የመጀመሪያዎቹ ሆነዋል።
ከ1.3 ቢሊዮን በላይ ሕዝብን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል የታሰበውን ይህንን ክትባት ያስጀመሩት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሮናቫይረስ ህሙማንን ለማከም በቀዳሚነት ለተሰለፉ የጤና ባለሙያዎች ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
"በዓለም ትልቁን የክትባት ዘመቻ እየጀመርን ነው፤ ይህም ምን ያህል አቅም እንዳለን ለዓለም የሚያሳይ ነው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ዛሬ [ቅዳሜ] ጠዋት ለአገራቸው ሕዝብ ባደረጉት ንግግር አመልክተዋል።
ጨምረውም አገራቸው ሕዝቧ የቫይረሱን መከላከያ ክትባት እንዲያገኝ በሞባይል መተግበሪያ አማካይነት ክትትል እንደምታደርግና ይህም ማንም ሰው ክትባቱን ሳያገኝ እንዳይቀር መንግሥት ክትትል ለማድረግ ይረዳዋል ብለዋል።
የጤና ባለሙያዎች በአስቸጋሪ ጊዜ ሕዝቡ ተስፋን እንዲያይ ማድረጋቸውን በመግለጽ "ለረዥም ጊዜ ከቤተሰባቸው ተለይተው የሌሎችን ሕይወት ለመታደግ ሕይወታቸውን ሰጥተዋል" በማለት ለባሙያዎቹ አክብሮትን ለመግለጽ የመጀመሪያው ክትባት እንዲሰጣቸው መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ለዚህ የክትባት ዘመቻም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የተፈቀዱት ኮቪድሺልድ እና ኮቫክሲን የተሰኙ ክትባቶች በመላ አገሪቱ ተዳርሰዋል።
ክትባቶቹ በመጀመሪያ ለጤና ሠራተኞች እና የኮሮናቫይረስ ህክምና ለሚሰጡ የህክምና ባመሉያዎች እንዲሁም ለሌሎች ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይደርሳል።
ከአሜሪካ በመቀጠል ሕንድ በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኮቪድ-19 የያዛቸውን ሰዎችን አስመዝግባለች።
ሕንድ በያዘችው ዕቅድ መሠረት በመጀመሪያው ዙር 10 ሚሊዮን የሚገመቱ የጤና ባለሙያዎች ክትባቱን የሚወስዱ ሲሆን ፖሊሶች፣ ወታደሮች፣ የማዘጋጃ ቤት እና ሌሎችም ሠራተኞችም ክትባቱን እንደሚያገኙ ተነግሯል።
በመቀጠልም ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ እና ከ50 በታች ሆነው ከባድ የጤና እክሎች ያሉባቸው ይከተባሉ ተብሏል።
ወደ 900 ሚሊዮን ገደማ የመራጮችን ስም ዝርዝር የያዘው የሕንድ የምርጫ መዝገብ ብቁ የሆኑ ተከታቢዎችን ለመለየት ጥቅም ላይ ይውላል።
መንግሥት እስከ ነሐሴ መጀመሪያ ድረስ 300 ሚሊዮን ሰዎችን ለመከተብ አቅዷል። ይህም በመንግሥት በሚተዳደሩ የጤና እንክብካቤ ማዕከላት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች፣ በአዳራሾች፣ በማዘጋጃ ቤቶች እና በሌሎች በአዳራሾች ውስጥ ይከናወናል።
በሕንድ ያሉ በርካታ ሆስፒታሎች የመጀመሪያውን ክትባቱ ለመስጠት ዝግጁ ሆነው እየተጠባበቁ ነው።
የሕንድ መድኃኒት ተቆጣጣሪ ተቋም አስካሁን ለሁለት ክትባቶች እውቅና ሰጥቷል። እነሱም ኮቪድሺልድ እና ኮቫክሲን ይባላሉ።
ነገር ግን የኮቫክሲን ውጤታማነት ላይ ስጋቶች ተፈጥረዋል፤ ምክንያቱም የሦስተኛ ክሊኒካዊ ሙከራዎች ከመጠናቀቃቸው በፊት ስለመጣ ነው ተብሏል። ተቆጣጣሪውና አምራቹ ግን ክትባቱ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑንና ውጤታማነቱ እስከ የካቲት ወር ድረስ ይፋ ይሆናል ብለዋል።
ሁለቱም ክትባቶች በ28 ቀናት ልዩነት ሁለት ጊዜ ይሰጣሉ። ሁለተኛው ዙር እንደማጠናከሪያ ሲሆን የመከላከል አቅሙ ከመጀመሪያው ክትባት በኋላ ቢጀምርም ሁለተኛው ከተሰጠ ከ14 ቀናት በኋላ ወደ ሙሉ ውጤቱ ይደርሳል ተብሏል።
የክትባቶቹ የሚያገኙ ሰዎች ሁኔታ በኤሌክትሮኒክስ ክትትል የሚደረግባቸው ሲሆን የመጀመሪያዎቹን ክትባቶች የሚወስዱ ወደ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ቀድመው ተመዝግበዋል። ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች ክትባቱን ለመስጠት ሰልጥነዋል።
ክትባቶቹ በፈቃደኝነት የሚሰጡ ሲሆን ተከታቢዎችም ሁለቱንም ዙር ካጠናቀቁ በኋላ የክትባት የምስክር ወረቀት ይሰጣቸዋል።
በሕንድ ታዋቂ የሆኑት የክትባት ኤክስፐርት ዶ/ር ጋጋንዴፕ ካንግ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "የሕንድ የክትባት ፕሮግራም ከአብዛኞቹ አገራት እጅግ በተሻለ ሁኔታ እንደሚከናወን እጠብቃለሁ" ብለዋል።
በዋና ከተማዋ ዴልሂ ትልቁ የኮቪድ-19 ሆስፒታል ውስጥ የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ፋራ ሁሴን ዛሬ ቅዳሜ የመጀመሪያዎቹን ክትባቶች ከሚያገኙት መካከል ናቸው።
"በሥራ ላይ በመሆን የቤተሰቤን ደኅንነት ለመጠበቅ መሞከሩ ረጅም እና ዋጋ የሚያስከፍል ጉዞ ነበር። ወላጆቼ እና አያቶቼ ልጆቼን በመንከባከብ ስለረዱኝ እኔም ከልጆቼ ተለይቼ የበሽታውን የመተላለፍ እድል ለማስቀረት መሥራት ነበረብኝ" ሲሉ ዶ/ር ሁሴን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ክትባቱ በሥራዬ ምክንያት ለቤተሰቦቼ ተጨማሪ ተጋላጭነትን እንዳልፈጥር ለመከላከል ይህ የመጀመሪያው እርምጃ ሲሆን፤ ይህም ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ። ይህን ከባድ ሸክም ከትከሻዬ ላይ ያነሳልኝ" ብለዋል።