ኮሮናቫይረስ፡ ሐሰተኛ ዜና በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ደቡብ እስያውያንን የኮቪድ-19 ክትባት እንዳይወስዱ እያደረገ ነው ተባለ

ታትሟል

ሐሰተኛ ዜና በዩናይትድ ኪንግደም የሚኖሩ የተወሰኑ የደቡብ እስያ ማኅበረሰብ አባላት የኮሮናቫይረስ ክትባትን ላለመውሰድ እንዲያንገራግሩ እያደረገ ነው ሲሉ ሐኪሞች አስጠነቀቁ።

ዶ/ር ሀርፕረት ሱድ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የጤና አገልግሎት ዘርፍ የተሳሳቱ መረጃዎችን በሚያጣራው ቡድን ውስጥ ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባትን በሚመለከት የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች "በጣም አሳሳቢ ናቸው" ካሉ በኋላ "ይህንን ለማስተካከል እየሰራን ነው" ብለዋል።

ለሐሰተኛ መረጃዎቹ መስፋፋት እንደምክንያት የተጠቀሰው የባህልና የቋንቋ ተግዳሮት መኖሩን ነው።

በምዕራብ ሚድላንድስ የምትሰራ አንዲት ዶክተር ለቢቢሲ እንደተናገረችው የተወሰኑ ደቡብ እስያውያን የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባቱን አንወስድም ሲሉ አንገራግረዋል።

በእንግሊዝ የብሔራዊ ጤና አገልግሎት ውስጥ የሚሰሩት ዶ/ር ሱድ፣ እነዚህን ስለክትባቱ የሚነገሩ ሐሰተኛ መረጃዎች ለማስወገድ ከደቡብ እስያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች ጋር እየሰሩ ነው።

በርካቶቹ የሐሰተኛ መረጃዎች የሚያጠነጥኑት በክትባቱ ይዘት ዙሪያ ነው ተብሏል።

እነዚህ የማኅበረሰብ አባላት የእንስሳት ተዋጽኦ እንደማይመገቡ ስለሚታወቅ "ክትባቱ ከላምና ከአሳማ ሥጋ መሰራቱ" እንደተወራ ዶ/ር ሱድ ያስረዳሉ።

"በሁሉም የእምነት አባቶች ክትባቱ ተቀባይነት ማግኘቱንና ተከታዮቻቸውም እንዲወስዱት መፍቀዳቸውን በግልጽ ለማኅበረሰቡ አባላት መንገር አለብን" ብለዋል።

አክለውም ለማኅበረሰቡ በሚናገሩት ቋንቋ ተተርጉሞ የሚሰራጨው መረጃ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል መድረሱን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።

ስለዚህም በየማኅበረሰቡ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪና አርአያ የሆነ ግለሰብ እየፈለግን፣ አንዳቸው ለሌላኛቸው ትክክለኛውን መረጃ በማስተላለፍ የተሳሳተውን መረጃ እንዲቀለብሱ እየሰራን ነው ብለዋል።

ቢቢሲ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ ያያቸው የተወሰኑ የተሳሳቱ መረጃዎች ሐይማኖትን መሰረት ተደርገው የተሰራጩ ናቸው።

እነዚህ መልዕክቶች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት የእንስሳ ተዋጽኦን ይዟል የሚሉ ሲሆን፣ የአሳማ ሥጋ በማይበሉ ሙስሊሞች እና የበሬ ሥጋ በማይበሉ ሂንዱዎች ረገድ ይህ መረጃ በስፋት ተሰራጭቶ ተቀባይነት አግኝቷል።

ዶ/ር ሳማራ አፍዛል በምዕራብ ሚድላንድስ ዱድሊ ሰዎችን ስትከትብ "ሁሉንም ሕሙማን ለክትባት ወረፋ እንዲይዙ እንዲደረግ ለሠራተኞቹ ቢነገርም፣ ነገር ግን የደቡብ እስያ ተወላጅ የሆኑ አንዳንድ ሕሙማን ክትባቱን አንወስድም ማለታቸውን ሰምተናል"

"ቤተሰባቸውንና ጓደኞቻቸውን ባነጋገርንበትም ወቅት ያገኘነው መረጃም ተመሳሳይ ነው። እኔ ራሴ ጓደኞች አሉኝ፤ ቤተሰቦቹቼ ወይም አያቶቼ ክትባቱን እንዲወስዱ እንዳሳምንላቸው የሚጠይቁኝ" ስትል የገጠማትን ተናግራለች።

በሃምፕሻየር የውበት ባለሙያ የሆነችው ሬና ፑጃራ የሂንዱ እምነት ተከታይ ስትሆን በእንደዚህ አይነት ሐሰተኛ መረጃዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ገጿ መጥለቅለቁን ትናገራለች።

"ላልተማረ ሰው ግራ አጋቢ ነው። በዚያ ላይ ክትባቱ ከላም ሥጋ እንደተሰራ ሲገነጽ፤ ላም ደግሞ ለእኛ ቅዱስ በመሆኗ የሚረብሽ ነው" ብላለች።

100 መስጂዶች በኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ላይ የሚናፈሱ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመመከትና ማኅበረሰቦቻቸው ክትባቱን እንዲወስዱ ለማሳመን ጥምረት ፈጥረዋል።

እነዚህ መስጂዶች የአርብ ፀሎትን ለማስተማሪያነት ለመጠቀም ተስማምተዋል።

በቅርቡ በሮያል ሶሳይቲ ኦፍ ፐብሊክ ሄልዝ በተደረገ ጥናት ግማሽ ያህል ጥቁሮች፣ እስያውያን እና ሌሎች በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ሕዝቦች የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለመውሰድ ፈቃደኛ ናቸው ይላል።

ከ79 በመቶ ነጮች መካከል ደግሞ 57 በመቶዎቹ ለመውሰድ ፈቃደኛ መሆናቸውን በጥናቱ ላይ ተመልክቷል።