ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ ፡ የካሊፎርኒያው ዲዝኒላንድ መዝናኛ ቦታ የኮቪድ-19 ክትባት ማዕከል ሊሆን ነው
ታዋቂው በካሊፎርኒያ የሚገኘው ዲዝኒላንድ የመዝናኛ ፓርክ የኮቪድ -19 ክትባት መስጫ ማዕከል በመሆን ግልጋሎት ሊሰጥ እንደሆነ የአካባቢው ባለስልጣናት አስታወቁ።
በአገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመሩና ሆስፒታሎች ጫና እየበዛባቸው ባለበት ወቅት በግዛቱ ከሚከፈቱ በርካታ ትላልቅ የክትባት መስጫ ቦታዎች አንዱ በመሆን 'የምድራችን እጅግ አስደሳቹ ቦታ' በመባል የሚታወቀው ዲዝኒላንድ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል።
የበርካታ ሕዝብ መኖሪያ በሆነችው የአሜሪካዋ ግዛት ክትባቱን ለነዋሪወዎቿ በመስጠት ረገድ ወደ ኋላ ቀርታለች ተብሏል። እስከ አሁን ካሊፎርኒያ ለመስጠት ካዘጋጀችው ክትባት ውስጥ አንድ ሦስተኛው ብቻ ነው የተሰጠው።
በግዛቲቱ ውስጥ ሰኞ ዕለት በተደረጉ ምርመራዎች ከ40 ሺህ በታች አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መገኘታቸውንና 264 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሰበብ እንደሞቱ ተመዝግቧል።
የአገሪቱ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል መረጃ እንደሚያመለክተው ካሊፎርኒያ 100 ሺህ ነዋሪዎችን በመከተብ ከ50 ግዛቶች ውስጥ 42ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ተብሏል።
ካሊፎርኒያ ውስጥ ኦሬንጅ በሚባለው አካባቢ የሚገኘው ዲዝኒላንድ የመዝናኛ ስፍራ በግዛቱ የመጀመሪያው የክትባት ጣቢያ ይሆናል ሲል የአካባቢው አስተባባሪ አንድሪው ዶ ተናግረዋል። በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የመከተብ አቅምም ይኖረዋል ተብሏል።
ፓርኩ ካለፈው ዓመት ከመጋቢት አጋማሽ አንስቶ ለእንግዶች ተዘግቷል። ይህ ፓርክ በፍሎሪዳ ከሚገኘው ተመሳሳይ የመዝናኛ ስፍራው ዋልት ዲዝኒ ወርልድ በተቃራኒ ከሐምሌ ጀምሮ ለተወሰኑ እንግዶች ክፍት ሆኖ ቆይቷል።
ከዲዝኒ ላንድ በተጨማሪ የካሊፎርኒያው ገዢ ጋቪን ኒውሶም ለተመሳሳይ የክትባት ጣቢያነት የሚያገለግል ማዕከል በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በሎስ አንጀለስ ዶጀር ስታዲየም እንደሚከፈትም አስታውቀዋል።
ኒውሶም እንዳሉት "አሁን ያለው ስትራቴጂ በምንፈልገው ፍጥነት ወደ ዓላማችን እንደማያደርሰን እንገነዘባለን" ብለዋል።
"ለዚህም ነው አስተዳደሩ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ብቻ አይደለም ይህንን ለማድረግ ትልልቅ ጣቢያዎችን የምንከፍተው" ሲሉ ገልጸዋል።
የግዛቱ የክትባት ዘመቻ ትኩረት ያደረገው ከፍተኛ ትኩረት በሚደረግባቸው ለበሽታው ቀዳሚ ተጋላጭ ለሆኑት የጤና ሠራተኞችና ለረጅም ጊዜ በእንክብካቤ ተቋማት ለሚኖሩ አረጋዊያን ነው።
"ወርቃማዋ ግዛት" ተብላ በምትጠራው ካሊፎርኒያ በአሜሪካ ውስጥ ሦስተኛ ከፍተኛ የሞት መጠን የተመዘገበባት ግዛት ናት።
በግዛቲቱ በቫይረሱ ምክንያት ከ22,600 በላይ ሰዎች ወደ ሆስፒታል መግባታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
የሎስ አንጀለስ ከፍተኛ የኅብረተሰብ ጤና ጥበቃ ባለስልጣን ባርባራ ፎሬር እንዳሉት "በዚህ ሞገድ በቤተሰቦቻችንና በአካባቢያችን ሆስፒታሎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ግዛታችን በአስርተ ዓመታት ውስጥ ያጋጠመው እጅግ የከፋ አደጋ ነው" ብለዋል።
በተቀረው የአሜሪካ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ከሆነ አሜሪካ 22.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮቪድ -19 የተያዙ ሲሆን አስካሁን ከ376 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።