ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእስር ላይ የነበረቸው ብቸኛ የአሜሪካ መንግሥት የሞት ፍርደኛ ቅጣቷ ተግባራዊ ሆነ
በግድያ ወንጀል ሞት ተበይኖባት በአሜሪካ የፌደራል መንግሥት እስር ቤት ውስጥ የነበረችው ብቸኛዋ የሞት ፍርደኛ ሊሳ ሞንትጎምሪ ቅጣቷ ተግባራዊ ተደረገ።
ሊሳ እንዳትገደል ተጥሎ የነበረው ዕገዳ በአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከተነሳ በኋላ፣ በኢንዲያና ግዛት ውስጥ በቆየችበት እስር ቤት በመርዝ መርፌ ተወግታ የተገደለችው።
የሊሳ ሞንትጎምሪ ጠበቃዋ በልጅነቷ በጣም በሆነ ሰቆቃ ውስጥ ያለፈችና የአዕምሮ ጤና ችግር ያለባት መሆኑን በመግለጽ የሞት ፍርዱ ተግባራዊ እንዳይሆን በተከራከሩበት ጊዜ ጉዳይዋ ከፍተኛ ትኩረትን አግኝቶ ነበር።
የ52 ዓመቷ ሊሳ ከ15 ዓመታት በፊት ሚሲሪ ግዛት ውስጥ አንዲት ነፍሰጡር ሴትን አንቃ ከማሰቃየቷ በተጨማሪም፣ በአሰቃቂ ሁኔታ የመግደል ወንጀል በመፈጸሟ ነበር ሞት የተፈረደባት።
የወንጀሉ ሰለባ የነበረችው የ23 ዓመቷ ነፍሰጡር ቦቢ ጆ ስቲኔት በከፍተኛ ሁኔታ ደም ፈሷት ነበር ለሞት የተዳረገችው።
በሞንትጎምሪ ላይ ተግባራዊ የተደረገው የሞት ቅጣት ከ67 ዓመታት በኋላ በፌደራል መንግሥቱ የተፈጸመ የመጀመሪያው የሞት ፍርድ ሆኗል።
በሊሳ ሞንትጎምሪ ላይ የተፈጸመውን የሞት ፍርድ ሂደት የተመለከቱ የዓይን እማኞች እንደተናገሩት፣ ከመገደሏ በፊት ፊቷ ተሸፍኖ የነበረበት ጨርቅ ተነስቶላት በመጨረሻ የምትናገረው ነገር ካለ ተጠይቃ "የለኝም" በማለት ምንም ሳትናገር በመርዝ መርፌ ተገድላለች።
ህይወቷ ማለፉ ከተረጋገጠ በኋላ የሞት ፍርዱ ተግባራዊ እንዳይደረግ ሲሟገቱላት የነበሩት ጠበቃ ኬሊ ሄንሪ፣ በሊሳ የሞት ቅጣት ውስጥ የተሳተፉ በሙሉ "ሐፍረት ሊሰማቸው ይገባል" ብለዋል።
"ይህችን የተጎዳችን የአዕምሮ ጤና ችግር ያለባትን ሴት በሞት መቅጣት ፍትህን ከማስፈን በእጅጉ የራቀ ድርጊት ነው" ጨምረው ብለዋል።
ሊሳ ላይ የተፈጸመው ግድያ በመጀመሪያ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትና በኋላ ላይ ደግሞ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍርዱ እንዲፈጸም የመጨረሻ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ በአንድ ዳኛ ታግዶ ነበር።
ፍርድ ቤት በግለሰቧ የአዕምሮ ጤና ላይ ምርመራ እንዲደረግ አዞ የነበረ ሲሆን፤ ጠበቆቿም በአንጓሏ ላይ ከደረሰ ጉዳት ጋር መወለዷንና ከባድ የአዕምሮ ጤና ችግር እንዳለባት በመጥቀስ የሞት ቅጣቱ እንዳይፈጸም ተከራክረው ነበር።
የሊሳ ቤተሰብ አባላት እንዳሉት በልጅነቷ በአባቷ ወሲባዊና አካላዊ ጥቃት እንደደረሰባትና እናቷ ደግሞ ወደሌላ ቦታ በመውሰድ ስቃይ እንዲገጥማት እንዳደረገቻት ገልጸዋል።
ሊሳ ወንጀሉን በፈጸመችበት ጊዜ በከባድ የአዕምሮ ህመም ትሰቃይ እንደነበር ጠበቆቿ ተናግረዋል። ይህም በ41 ጠበቆችና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ተመስክሯል።
ነገር ግን የሟች ቤተሰቦችና ጓደኞቿ ሊሳ የፈጸመችው ግድያ እጅግ ዘግናኝ በመሆኑ የአዕምሮ ጤናዋ ጉዳይ ከግምት ሳይገባ የሞት ቅጣት እንደሚገባት ተከራክረዋል።