ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ ፡ በሞባይል ስክሪን ላይ የምናሳልፈው ጊዜና የዓይናችን ጤና በኮቪድ-19 ዘመን
ኮሮናቫይረስ ያስከተለውን የእንቅስቃሴ እገዳ ተከትሎ የሰዎች በስልክና በኮምፒውተር ስክሪን ላይ ያላቸው የቆይታ ጊዜ የጨመረ በመሆኑ ለዓይናቸው ደኅንነት መጠበቅ የ"20-20-20" ደንብን እንዲለማመዱ አንድ የዓይን ጤና በጎ አድራጎት መክሯል።
'ፋይት ፎር ሳይት' ለ20 ደቂቃዎች ስክሪን ላይ አንዳች ነገር እያደረጉ ከቆዩ በኋላ 20 ጫማ ርቀት ላይ ያለን ነገር ለ20 ሰከንድ መመልከት ይመክራሉ።
ከ2,000 ሰዎች መካከል ግማሾቹ ከኮቪድ-19 መከሰት በኋላ ከፍ ያለ ጊዜን ስክሪን ላይ እያጠፉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንድ ሦስተኛው (38 በመቶ) የሚሆኑት የዓይን ችግራቸው መባባሱን አንድ ጥናት አመልከቷል።
የዓይን ሐኪሞች ደግሞ እርዳታ ለሚገፈልጉ ሰዎች ሁሌም ክፍት ሆነው ቆይተዋል ሲል የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ገልጿል።
ነገር ግን በ2 ሺህ ጎልማሶች ላይ የተደረገው ጥናት እንዳመለከተው በቫይረሱ መያዝን ወይም ማሰራጨትን በመፍራት ከአምስቱ ውስጥ አንዱ ከወረርሽኙ በፊት እንደነበረው የዓይን ምርመራ የማድረግ ዕድሉ አነስተኛ ነው ብሏል።
የጥናቱ ተሳታፊዎች እንዳሉት የማንበብ ችግር፣ እንዲሁም ራስ ምታት፣ በተወሰነ የጭንቅላት ክፍል ላይ የሚከሰት ከባድ የራስ ምታት [ማይግሬን] እና ደካማ የማታ ዕይታ እንዳለባቸው ሪፖርት አድርገዋል።
ሰዎች መደበኛ የዕይታ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ማስታወስ እንደሚያስፈልግ እና "አብዛኞቹ የዓይን ሐኪሞች የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለባቸው ወቅቶችም ለቀጠሮ ክፍት ሆነው ቆይተዋል" ተብሏል።
የፋይት ፎር ሳይት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽሪን ክራውስ "የዓይን ችግር ከሚያስከትሉ ጉዳዮች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ቀደም ብሎ በመለየትና የመከላከል ዘዴዎችን በመተግበር ሊወገዱ ይችላሉ። መደበኛ የዓይን ምርመራዎች ብዙውን ጊዜ ምልክት የሌላቸውን የዕይታ ችግሮች ለይተው ማወቅ ያስችላሉ" ብለዋል።
በየመካከሉ ቀላል ዓይንን ከስክሪን ዕይታ ዞር በማድረግ እረፍት ማግኘት ዓይን ላይ የሚፈጠር ጫናን ለመከላከል ይረዳል ሲል የበጎ አድራጎት ድርጅቱ አመልክቷል።
የዓይን ሐኪሞች ቀጠሮዎች ተፈቅደዋል
በመንግሥት መመሪያ መሠረት ሰዎች በዕገዳ ወቅትም ቢሆን ለህክምና ቀጠሮ ከቤት መውጣት እና "ጉዳትን፣ ህመምን ወይም የመጎዳት አደጋን ማስወገድ" ይችላሉ ይላል።
የዓይን ህክምና ኮሌጅ አባላት ማንኛውም የዕይታ ለውጥ ወይም ችግር ላጋጠማቸው ሰዎች በእገዳው ጊዜ የዓይን እንክብካቤ መስጠቱን መቀጠል አለባቸው ብሏል።
መደበኛ ቀጠሮዎችም "አቅም በፈቀደ መጠንና ለህሙማን ጥቅም እስከሆነ ድረስ" በቀላሉ ሊመቻቹ ይገባል ይላል መመሪያው።
የዓይን ህክምና ክሊኒክ አማካሪ ፓራምዴፕ ቢልኩ እንደተናገሩት የኮሌጁ ጥናት የተወሰኑ ሰዎች በመጀመሪያው ዕገዳ ወቅት ዕይታቸው መታወኩን አስተውለዋል።
"ብዙ ሰዎች በስክሪኖች ፊት ብዙ ጊዜ ማሳለፋቸው ዕይታ ችግራቸውን እንዳባባሰው እንደሚያምኑ ያደረግነው ጥናት አሳይቷል" ብለዋል።
"መልካሙ ዜና እንዲህ ያሉት ችግሮች በዕይታ ላይ ዘላቂ ጉዳት የማያስከትሉ መሆናቸው ነው። ሆኖም ግን ዕይታዎ እንደተዳከመ ከተሰማዎት ወይም ዓይኖችዎ ሲቀሉ ወይም ህመም ሲሰማዎ በቅርብዎ የሚገኙ የዓይን ሐኪሞችን በስልክ ወይም በድረገጽ ላይ በማግኘት ማማከር ያስፈልጋል" ሲሉ ገልጸዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የጤናና ደኅንነት ሕግ አሠሪዎች ሠራተኞች በቀን ከአንድ ሰዓት በላይ ለሥራ ስክሪን መጠቀም ካለባቸው ለሠራተኞቻቸው የዓይን ምርመራ ማድረግ አለባቸው።
በበጋ ወቅት ቢያንስ 10,000 ያህል ሰዎች በብሪታንያ አስፈላጊ የሆነ የዓይን እንክብካቤ እንዳላገኙ ተልጿል።
አስከፊው ጉዳይ የሮያል ብሔራዊ ዓይነ ስውራን ኢንስቲትዩት በወረርሽኙ ወቅት ሆስፒታል መሄድን በመፍራት አንዳንድ ሰዎች ዕይታቸውን የማጣት አደጋ ተጋርጦባቸዋል የሚል ስጋት እንዳለው ተናግሯል።
የሮያል ኮሌጅ የዓይን ህክምና ባለሙያዎች ቃል አቀባይ "በዕይታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ የተመለከቱ ሰዎች የዓይን ሐኪም ምክር መጠየቁ እና ለውጦቹ የዓይን ሐኪም ተጨማሪ ምርመራ የሚፈልግ መሆኑን መወሰን አስፈላጊ ነው" ብለዋል።