ኮሮናቫይረስ፡ ቻይና 11 ሚሊዮን ሰው በሚኖርባት ከተማ ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለች

ታትሟል

ቻይና በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ በምትገኘውና የ11 ሚሊዮን ሰዎች መኖሪያ በሆነችው ሺጂያዡዋንግ ከተማ ውስጥ ከ100 በላይ አዲስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ስላገኘች የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለች።

በዚህም ነዋሪዎች ከተማዋን ለቅቀው እንዳይወጡ የተከለከሉ ሲሆን ትምህርት ቤቶችም ተዘግተዋል።

ነዋሪዎች ተመርምረው ውጤታቸውን ማወቅ እንዲችሉ በከተማዋ ከ500 በላይ የመመርመሪያ ቦታዎች ተከፍተዋል።

በከተማዋ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር በቻይና ለተከታታይ አምስት ወራት ከተመዘገበው አሃዝ ውስጥ ከፍተኛው ነው። ቻይና የወረርሽኙ ምልክት በታየባቸው አካባቢዎች ፈጣንና ጠንካራ እርምጃ መውሰድ ስለቻለች የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር ችላለች።

ምንም እንኳን በአንጻራዊነት ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም፣ በአገሪቱ በአንድ ስፍራ ላይ ሰብሰብ ያሉ ሰዎች በበሽታው ተይዘው በመገኘታቸው፣ መንግሥት የጅምላ መርመራ በማድረግ ህሙማኑን መለየት ችሏል።

ከተማዋ ሺጂያዡዋንግ በምትገኝበት ሄቤይ ግዛት ውስጥ ሐሙስ ዕለት በተደረገው ምርመራ 120 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ከአንዱ በስተቀር ቀሪዎቹ የሚኖሩት ከተማዋ ውስጥ ነው። በቀሪው የቻይና ክፍል ግን ቫይረሱ የተገኘው 22 ሰዎች ላይ ብቻ ነው።

የኮሮናቫይረስ ባለፈው ዓመት መጀመሪያ የተገኘው ዉሃን በምትባለው የቻይና ከተማ ውስጥ ነበር።

በሺጂያዡዋንግ ከተማ ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለው የቻይናውያን አዲስ ዓመት ሊከበር አንድ ሳምንት ብቻ ሲቀረው ነው።

በዚህ በዓል ላእ በርካታ ቻይናውያን ወደቤተሰቦቻቸው ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሺጂያዡዋንግ ከተማ ውስጥ በርካታ ሰው በበሽታው ተይዞ የተገኘባት የጋዎቼንግ አካባቢ ነዋሪዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው እንዳይወጡ የተከለከሉ ሲሆን፤ ሌሎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች ደግሞ ከከተማዋ ወጥተው መሄድ አይችሉም።

ትራንስፖርትን በተመለከተም የአውቶብስ መጓጓዣ በመቆሙ አገልግሎት የማይሰጥ ሲሆን የአየር በረራዎችም ተሰርዘዋል።

ባለስልጣናት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በሰጡት ጠንካራ ትኩረት የተነሳ ከከተማዋ የሚወጡና ወደ ከተማዋ የሚገቡ የፖስታ መልዕክት አገልግሎቶች ለሦስት ቀናት እንዲቋረጡ አድርገዋል። ፖሊሶችም የጥንቃቄ አልባሳት አድርገው የተጣለውን ገደብ በጥብቅ እያስፈጸሙ ነው።

ዕለታዊው መንግሥታዊ ጋዜጣ 'ቻይና ዴይሊ' እንደዘገበው በርካታ ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው የከተማዋ ክፍል ጋዎቼንግ ሦስት ባለስልጣናት "በቸልተኝነት" ተቀጥተዋል።

"የወረርሽኙን መስፋፋት ለመቀነስ በተቻለ ፍጥነት መንደሮች በበሽታው የተያዙ ሰዎችን በምርመራ ማወቅ፣ ሪፖርት ማድረግ፣ መለየትና ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ አለባቸው" ሲሉ አንድ የአገሪቱ የጤና ባለስልጣን ተናግረዋል።

በሺጂያዡዋንግ ከተማ የሚገኙ አምስት ሆስፒታሎች የኮቪድ-19 ህሙማንን እንዲያስተናግዱ የተዘጋጁ ሲሆን ሌሎች ሦስት ሆስፒታሎች ደግሞ በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ መደረጉን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ተናግረዋል።

መጀመሪያ በሽታው ዉሃን ውስጥ ከተቀሰቀሰ በኋላ ቻይና በአንድ ስፍራ ላይ በርካታ በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎችን ስታገኝ እና የእንቅስቃሴ ገደብ ስትጥል ይህ የመጀመሪያ አይደለም።

በጥቅምት ወር ላይ ዘጠኝ ሚሊዮን ነዋሪ ያለት ኪንግዳዎ የተባለችው ከተማ ውስጥ በርካታ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ በአምስት ቀናት ውስጥ ነዋሪዎቹ ምርመራ ተደርጎላቸው ነበር። በከተማዋ የተገኘው ቫይረስ የተስፋፋው ከውጪ አገራት የመጡ ህሙማን ከሚታከሙበት አንድ ሆስፒታል ነበረ።

በተመሳሳይ ወር ዢንጂያንግ በምትባለው ግዛት ውስጥ ባለችው የካሽጋር ባለስልጣናት ወረርሽኝ መከሰቱ ከታወቀ በኋላ 4.7 ሚሊዮን ሰዎች እንዲመረመሩ አድርገዋል።