ኮቪድ-19፡ የኮሮናቫይረስን መነሻ ለማጥናት ዓለም አቀፍ የተመራማሪዎች ቡድን ወደ ቻይና ሊያመራ ነው

ታትሟል

የኮቪድ -19ን መነሻ ለማጥናት አስር ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችን የያዘ ቡድን በሚቀጥለው ወር ወደ ቻይና ዉሃን እንደሚያቀና የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

ቻይና በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ፈቃደኛ አልነበረችም።

በዚህም ምክንያት የዓለም ጤና ድርጅት ከተማዋ ውስጥ ገብቶ ምርመራ ለማካሄድ እንዲፈቀድለት ለማግባባት ወራቶችን ወስዶበታል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በውሃን ከተማ የእንስሳት መሸጫ ገበያ እንደተነሳ ይታመናል።

ይሁን እንጂ የበሽታውን ምንጭ ለመፈለግ የሚደረገው ጥረት በተለይ ከአሜሪካ ጋር እሰጥ አገባን አስከትሏል።

የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ቻይና መጀመሪያ ላይ ወረርሽኙ ሲከሰት ለመደበቅ ሞክራለች ሲሉ ይከሳሉ።

ለምርምሩ ወደ ዉሃን ከሚያቀኑት ተመራማሪዎች አንዱ፤ የዓለም ጤና ድርጅት ምርምሩን የሚያካሂደው ለወቀሳ ሳይሆን ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን ለመከላከል እንደሆነ ለአሶሽየትድ ፕረስ ተናግረዋል።

የጀርመኑ ሮበርት ኮች የጥናት ተቋም ተመራማሪው ዶክተር ፋቢያን ሊንደርትዝ "ምርምሩ ለወረርሽኙ ጥፋተኛ የሆነውን አገር ለመፈለግ ሳይሆን፤ ምን እንደተከሰተ ለመረዳት መሞከር እና በእነዚያ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን አደጋ መቀነስ እንደሚቻል ለማየት ነው" ብለዋል።

ተመራማሪው አክለውም የምርምሩ ዋና ዓላማ ቫይረሱ መቼ መዛመት እንደጀመረ እና መነሻው ዉሃን ይሁን አይሁን ለማወቅ እንደሆነ አስረግጠው ተናግረዋል።

ይህ ዓላማም በአራት ወይም በአምስት ሳምንታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው የት እና መቼ ነበር?

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተገኘበት በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት፤ ቫይረሱ በቻይናዋ ሁቤ ግዛት ዉሃን ከተማ በአሳ እና ስጋ መሸጫ ገበያ የታየ ሲሆን ከእንስሳት ወደ ሰው የተላለፈውም እዚሁ እንደሆነ ተጠቁሟል።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ ባለሙያዎች ሌላ ቦታ ተከስቶ ቢሆንስ? ምን አልባት እዚያ ጎልቶ ታይቶ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ አላቸው።

ጥናቶች ሰዎችን የሚያጠቃው ኮሮናቫይረስ ለአስርት ዓመታት በሌሊት ወፎች ውስጥ ሳይታወቅ ሳይዛመት እንዳልቀር ያመለክታሉ።

ባሳለፍነው ዓመት ታህሳስ በውሃን ሆስፒታል ይሰራ የነበረው ቻይናዊው ዶክተር ሊ ዌንሊያንግ አዲስ ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችል የሕክምና ባለሙያዎችን ለማስጠንቀቅ ሞክሮ ነበር።

ነገር ግን 'ሐሰተኛ አስተያየት' መስጠቱን እንዲያቆም በፖሊስ ተነግሮት፤ 'አሉቧልታ በማዛመት' ምርመራ ሲደረግበት ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ዶክተር ሊ የካቲት ወር ላይ በከተማዋ ታማሚዎችን ሲያክም በኮሮናቫይረስ ተይዞ ሕይወቱ አልፏል።

ከዚያም ሚያዚያ ወር ላይ ቫይረሱ በዉሃን ከሚገኝ ቤተ ሙከራ ወጥቶ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬዎችና ክሶች መውጣት ጀመሩ።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የወጡ መረጃዎች እዚያ ያሉ የኤምባሲ ባለሥልጣናት ለሕይወት ደህነንነታቸው ተጨንቀው እንደነበር አመላክተው ነበር።

የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ዳሬክተር መስሪያ ቤትም ወረርሽኙ የተከሰተው በእንስሳ ንክኪ ወይም በቤተ ሙከራ እንደሆነ ለማወቅ ምርመራ እያደረጉ እንደነበር በወቅቱ አስታውቆ ነበር።

በቅርቡ የቻይና መገናኛ ብዙኃን ኮቪድ-19 የተነሳው ከቻይና ውጭ እንደሆነ ዘግቧል።

ይሁን እንጂ የዘርፉ ተንታኞች "ሪፖርቱ መሰረት የለውም፤ ዘመቻው ቤጂንግ ውስጥ ያሉ አመራሮች፤ ወረርሽኙ በአገሪቱ ዓለም አቀፍ ዝና ላይ ስለሚያሳድረው ተፅዕኖ ያላቸውን ጭንቀት የሚያንፀባርቅ ነው" ሲሉ አጣጥለውታል።