ኮሮናቫይረስ ፡ ትምህርት ቤቶቿን በከፈተችው ኬንያ መምህራን ስጋት አለን እያሉ ነው

ዛሬ ትምህርት ከጀመሩ ተማሪዎች መካከል
የምስሉ መግለጫ, ዛሬ ትምህርት ከጀመሩ ተማሪዎች መካከል
ታትሟል

የኬንያ ብሔራዊ የመምህራን ኅብረት ኃላፊ ዊልሰን ሶሲዮን በአገሪቱ ትምህር ቤቶች ዛሬ መከፈታቸውንተከትሎ በተማሪዎችና በመምህራን ደኅንነት ዙሪያ ስጋት እንዳላቸው ገልፈዋል።

ኃላፊው ለቢቢሲ እንደተናገሩት ለኮሮናቫይረስ ደኅንነት የተወሰዱ እርምጃዎች የዝግጅት ደረጃን "አነስተኛ" ሲሉ ገልጸውታል።

ሶሲዮን እንዳሉት ከአዳሪ ትምህርት ቤቶች በበለጠ ተማሪ ያላቸው አብዛኛዎቹ የቀን ትምህርት ቤቶች ለእጅ መታጠቢያ የሚሆን የውሃ አቅርቦት የላቸውም።

መንግሥት የሙቀት መለኪያዎች፣ የንጽህና መጠበቂያዎች እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለመግዛት የሚውል ገንዘብ ለትምህርት ቤቶች አለቀቀም ብለዋል።

"እንደዚህ አይነት መመሪያዎች ለትምህርት ቤቶች ተሰጥው የገንዘብ ድጋፍ ሳይሰጣቸው ሲቀር ... እንዴት ሊተገብሩት ይችላሉ?" ሲሉ ተይቀዋል።

የኬንያ መንግስት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል መምህራን ርቀታቸውን እንዲጠብቁ እና የንፅህና አጠባበቅ መመሪያዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ለበርካታ ወራት ከትምህርት ገበታቸው ውጪ ሆነው የቆዩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኬንያውያን ታዳጊ ተማሪዎች ወደ መጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ዛሬ ተመልሰዋል።

የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎች ትምህርታቸውን በጥቅምት ወር የጀመሩ ሲሆን በፈረንጆች ገናና አዲስ ዓመት ሰበብ ትምህርት ተቋርጦ ቆይቷል።

የአገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚከሰት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል መመሪያዎችን አውጥቷል።

መመሪያው መምህራን በመማር ማስተማሩ ሂደት የዛፍ ጥላን ጨምሮ አካላዊ ርቀትን ለማስጠበቅ ያስችላሉ ያሏቸውን ክፍት ቦታዎች እንዲጠቀሙ መክሯል።

ወላጆችም ለልጆቻቸው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲገዙ የተጠቁ ሲሆን መንግሥት ደግሞ ለችግረኛ ተማሪዎች የተወሰኑትን እንደሚያቀርብ አሳውቋል።

እድሜያቸው ከ58 ዓመት በላይ የሆኑና ቀደም ያለ የጤና ችግር ያለባቸው መምህራን ከቤታቸው ሆነው ወይም ከክፍል ውጪ ባሉ ቦታዎች ላይ እንዲያስተምሩ ጠይቋል።

ወረርሽኙ መከሰቱን ተከትሎ በመላው አገሪቱ ተጥሎ የነበረውን የሰዓት እላፊ ገደብ ፕሬዝደንቱ ኡሁሩ ኬንያታ ለተጨማሪ ሦስት ወራት ባለበት እንዲቆይ መደረጉን እሁድ ዕለት አሳውቀዋል።

ኬንያ አስካሁን ድረስ 96,802 በበሽታው የተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን 1,685 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን ማጣታቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።