ኮሮናቫይረስ፡ ደቡብ አፍሪካ በየካቲት ወር የኮቪድ-19 ክትባት ለመስጠት ተስፋ አድርጋለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታትሟል
በኮቪድ-19 ክፉኛ የተጎዳችው ደቡብ አፍሪካ በየካቲት ወር ክትባት ሊደርስልኝ ይችላል አለች። ነገር ግን ይህ የሚወሰነው ከመድኃኒት አምራቾች ጋር እየተደረገ ያለው ንግግር ስኬታማ ከሆነ ብቻ ነው ብላለች።
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በትንሹ የሕዝቡን 67 ከመቶ ለመከተብ ነው ያቀደው። ይህም 40 ሚሊዮን ለሚደርስ ሕዝብ ክትባት ማድረስን ይጠይቃል።
የጤና ሚኒስትሩ ዝዌሊ ሚክሄዚ ትናንት እሑድ እንደተናገሩት ክትባቱ ደቡብ አፍሪካ እንደደረሰ በከፍተኛ ፍጥነት የክትባት ዘመቻው ይጧጧፋል ብለዋል።
የጤና ሚኒስትሩ እንዳሉት አገራቸው ከሁሉም የክትባት አምራች ኩባንያዎች ጋር ንግግር እያደረገች ነው። ይሳካል ብለውም ተስፋን አሳድረዋል።
ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ከ1 ሚሊዮን በላይ የኮቪድ ታማሚዎችን በማስመዝገብ የመጀመርያዋ አገር ሆናለች።
ካለፈው ሳምንት ወዲህ በዝርያው ለየት ያለና በአጭር ጊዜ ውስጥ የመዛመት ባህሪ ያለው የኮቪድ ዓይነት በደቡብ አፍሪካ ከተገኘ ወዲህ ከፍተኛ ድንጋጤ ተፈጥሮ ቆይቷል።
አሁን ደቡብ አፍሪካ አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ የሚጠጉ ዜጎች በኮቪድ ተጠቅተዋል። 30ሺህ ሚሆኑት ደግሞ ሞተዋል።








