ኮሮናቫይረስ ፡ የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የኮቪድ-19 ክትባት ለሁሉም እንዲዳረስ አሳሰቡ

ሊቀ ጳጳሱ ይህን ያሉት የፈረንጆቹን የገና በዓል አስመልክተው ለመጀመሪያ ጊዜ በኦንላይን ባስተላለፉት መልዕክት ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ የኮሮናቫይረስ ክትባት ገደብ ሳይኖረው ለሁሉም እንዲዳረስ ለዓለም መሪዎች ጥሪ አቀረቡ።

ሊቀ ጳጳሱ ይህን ያሉት የፈረንጆቹን የገና በዓል አስመልክተው ለመጀመሪያ ጊዜ በኦንላይን ባስተላለፉት መልዕክት ነው። በመልዕክታቸውም የኮቪድ-19 ሕክምና እንዳይዳረስ አጥር መሰራት እንደሌለበት አሳስበዋል።

ሊቀ ጳጳሱ ዓመታዊውን መልዕክታቸውን ለሮም ከተማና ለዓለም ያደረሱት ከዚህ ቀደም እንደተለመደው ሰዎች በተሰበሰቡበት በቫቲካን ከሚገኘው ከቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል ቤተክርስቲያን በረንዳ ላይ አይደለም። ቫቲካን ውስጥ በሚገኝ ቻምበር አትሮኖስ ላይ ቆመው ነበር መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።

የፖፕ ፍራንሲስ ማሳሰቢያ የመጣው ድሃ አገራትን ለመጉዳት ሃብታም አገራት በርካታ የኮሮናቫይረስ ክትባቶችን ገዝተው እያከማቹ ነው የሚለው ዜና ከተሰማ በኋላ ነው።

ፖፕ ፍራንሲስ "የክትባትና የህክምና ተደራሽነት ለሁሉም እንዲረጋገጥ፤ ፈጣሪ ከጤና ጥበቃ ጀምሮ የፖለቲካና የመንግሥት መሪዎች ዓለም አቀፍ የትብብር መንፈስን ያድስ" ሲሉም ተማፅነዋል።

አክለውም "በዚህ ድንበር በማያውቅ አስቸጋሪ ሁኔታ አጥር ማበጀት አንችልም፤ ሁላችንም በአንድ ጀልባ ውስጥ ነው ያለነው" ብለዋል።

ሊቀ ጳጳሱ የጤና ቀውሱ ያመጣው መዘዝ ዓለም አቀፍ አንድነት ከምንም በላይ መሆኑን እንዳሳየም ተናግረዋል።

የሥነ ምህዳር ቀውስ፣ የኢኮኖሚ ችግር እና የማህበራዊ ሚዛን መዛባት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መባባሱንም በመጥቀስ፤ "እንደ እህትና ወንድም እርስ በርስ መደጋገፍ በጣም አስፈላጊ ነው" ሲሉ መክረዋል።

ሊቀ ጳጳሱ አክለውም በወረርሽኙ በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ሳቢያ በቤት ውስጥ ጥቃት የሚሰቃዩ ሴቶችን በመለየትና ለተጎዱትም ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል።

ፖፕ ፍራንሲስ በሶሪያ፣ የመን፣ ሊቢያ፣ ንጎሮካራብህ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ካሜሩንና ኢራቅ እርቅና ሰላም እንዲወርድም ጥሪ አቅርበዋል።

ሊቀ ጳጳሱ በመጪው መጋቢት ኢራቅ ይጎበኛሉ ተብሎም ይጠበቃል።