ኮሮናቫይረስ ፡ ሩሲያ የኮቪድ-19 ክትባትን በመዲናዋ ሞስኮ መስጠት ጀመረች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሩሲያ መዲና ሞስኮ የኮቪድ-19 ክትባት መስጠት ተጀመረ።
ሞስኮ የሚገኙ የሕክምና መስጫዎች ለበሽታው በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ከሆኑ ሰዎች ጀምሮ ክትባቱን እንደሚሰጡ ተገልጿል።
ሩሲያ ባለፈው ነሐሴ ላይ ይፋ ያደረገችው ስፑትኒክ 5 የተባለው ክትባት፤ 95 በመቶ ውጤታማ እንደሆነና ጉልህ የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌለው ተነግሯል።
በእርግጥ ክትባቱ አሁንም ሰዎች ላይ እየተሞከረ ነው።
የመጀመሪያውን ዙር ክትባቱን ለመውሰድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተመዝግበዋል።
ሩሲያ ምን ያህል ክትባት ማምረት እንደምትችል ግልጽ ባይሆንም፤ አምራቾች እስከ ዓመቱ መገባደጃ ሁለት ሚሊዮን ጠብታ እንዲያዘጋጁ ይጠበቃል።
ክትባቱ ለማን ይሰጣል?
13 ሚሊዮን ሰዎች የሚኖሩባት የሞስኮ ከተማ ከንቲባ ሰርጌ ሶቢያን እንዳሉት፤ ክትባቱ ለማኅበረሰብ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ለጤና ባለሙያዎች እና ለትምህርት ቤት ሠራተኞች ይሰጣል።
ተጨማሪ ክትባቶች ሲመረቱ ለተቀረው ማኅበረሰብ እንደሚዳረስ ከንቲባው ጠቁመዋል።
ከላይ በተዘረዘሩት የሙያ መስኮች የተሰማሩና እድሜያቸው ከ18 እስከ 60 የሆኑ ዜጎች በድረ ገጽ ተመዝግበዋል። በሞስኮ ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት የክትባቱን አገልግሎት የሚሠጡ 70 ማዕከሎች ተከፍተዋል።
ክትባቱ የተሰጣቸው ባለፉት 30 ቀናት የመተንፈሻ አካል ህመም የገጠማቸው፣ የከፋ የጤና እክል ያለባቸው፣ ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች እንደሚለዩ ተገልጿል።
ሕዝቡ ምን አለ?
ክትባቱን በተመለከት የሕዝቡ ስሜት የተደበላለቀ ነው።
የከተማው ነዋሪ ኢጎር ኪቮቦኮቭ "የበሽታውን ስርጭት ሊቀንስ ስለሚችል ደስ ብሎኛል" ሲል ለሮይተርስ ተናግሯል።
ሌላው ነዋሪ ሰርጌ ጊሻን ግን ክትባቱን ለመውሰድ አላሰብኩም ብሏል።
"ሂደቱ ረዥም ጊዜ ነው የሚወስደው። ያለው ክትባት ደግሞ ጥቂት ነው። ሌላው ሰው ይከተብ። እኔ እንኳን እተርፋለሁ ብዬ አስባለሁ።"
ሩሲያ ውስጥ እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከ2.3 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ሲሆኑ፤ 41,730 ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ ሰበብ ሞተዋል።
ሞስኮ ቫይረሱ በስፋት ከተሰራጨባቸው ከተሞች አንዷ ናት። በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ በቫይረሱ የሚያዙና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ይመዘገባሉ።
በመላው ሩስያ የሚገኙ ሆስፒታሎች የሚያስተናግዱት ህሙማን ቁጥር ከአቅማቸው በላይ ሆኗል።
ይሁን እንጂ ሩሲያ አገር አቀፍ የእንቅስቃሴ ገደብ እንደማትጥል አስታውቃለች።
የሞስኮ ከንቲባ ግን ባለፈው ወር ለመጠጥ ቤቶች የመክፈቻና የመዝጊያ ሰዓት ገድበዋል። የከፍተኛ ትምህርት በርቀት እንዲሰጥና የስፖርት ክንውኖች እንዲቀነሱም ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
















