አፈር የተደረመሰባቸውን የዚምባብዌ ማዕድን ቆፋሪዎችን ሕይወት አድን ስራ እየተከናወነ ነው ተባለ

ታትሟል

በሰሜናዊ ዚምባብዌ ከጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ማዕደን ሲያወጡ አፈር የተደረመሰባቸው ማዕድን ቆፋሪዎችን ሕይወት የመታደግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተዘገበ።

መንግሥት ሕገ-ወጥ ማዕደን አውቺዎቹ ማዕድን ፍለጋ ላይ ሳሉ አፈር የተደረመሰባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 30 እንደሚተጋ ይገመታል ብሏል። የነብስ አድን ስራው በፍጥነት እየተከናወነ እንደሆነም ተገልጿል።

በዚምባብዌ ያለው ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር እና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ በሕገ-ወጥ መልኩ ሰዎች በማዕድን ፍለጋ ቁፋሮ ላይ እንዲሰማሩ ማድረጉ ይነገራል።

በሕገ-ወጥ ማዕድን ቁፋሮ ላይ የሚሰማሩ ዜጎችም በቂ እና አስፈላጊ የሚባሉ የደህንነት መሳሪዎች የሏቸውም የደህንነት መመሪያዎችንም አይከተሉም ተብሏል።

በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ የዚምባብዌ ዜጎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ እንደሚገኝም ተገልጿል።

የአካባቢው ባለስልጣነት እንዳሉት እስካሁን 6 ሰዎች ከአደጋው ማዳን የተቻለ ቢሆንም ከ20 ያላነሱ ማዕድን ቆፋሪዎች አሁንም መውጣት አቅቷቸው ይገኛሉ።

አደገኛ በሆነው ቁፋሮ ምንም አይነት የደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ሳይጠቀሙ ማዕድን የሚቆፍሩ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ አደጋ መድረስ የተለመደ ነው። ለአደጋዎቹ ዋነኛ ምክንያቶች ደግሞ የድማሚት ፍንዳታዎች እና ድንገተኛ ጎርፍ ናቸው።

ዚምባብዌ በፕላቲኒየም፣ አልማዝና ወርቅ የበለጸገች አገር ነች። በአነስተኛ ደረጃ ወርቅ የሚያወጡ ሰዎች በአገሪቱ ከሚመረተው ወርቅ ግማሹን ያበረክታሉም ተብሏል።