ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራናዊው ዲፕሎማት በፈረንሳይ የቦምብ ጥቃት በማሴር ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው
በፈረንሳይ በኢራን መንግሥት ላይ በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የቦምብ ጥቃት ለማድረስ አሲረዋል የተባሉት ኢራናዊ ዲፕሎማት እና ትውልደ ኢራናዊያን የሆኑ ጥንዶች ዛሬ በቤልጄም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተባለ።
ትውልደ ኢራናውያን የቤልጄም ዜጎች የሆኑት ባል እና ሚስት ከሚኖርበት አንትዌራፕ ከተማ ለሽርሽር በማለት ወደ ላክሰምበርግ ከተማ መጓዛቸውን የቤልጄም ፖሊስ አስታውቋል።
አሚር ኤስ አንኣና ሲሜህ ኤን ተብለው የተጠሩት ባለትዳሮች፤ በላክስምበርግ ከተማ በሚገኝ አንድ ምግብ ቤት ውስጥ እድሜው በ40ዎቹ መጨረሻ ያለ ሰው ማግኘታቸውን ተነግሯል። ጥንዶቹ ከዚህ ግለሰብ አንድ ጥቅል ከተቀቡ በኋላ ወደ መኖሪያ አገራቸው ቤልጄም መመለሳቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
የጥንዶቹ ሙሉ እንቅስቃሴ በአውሮፓ ደህንነት ባለሙያዎች ክትትል ስር እንደነበረ ተጠቁሟል። ጥንዶቹ በምግብ ቤት ውስጥ አገኙት የተባለው ግለሰብ በቬይና ኦስትሪያ የኢራን ኤምባሲ ውስጥ የሚሰራ ኢራናዊው ዲፕሎማት አሳዶላህ አሳዲ ነው ተብሏል።
ዲፕሎማቱ ለጥንዶቹ የሰጣቸው ጥቅል፤ 1 ኪ.ግ የሚመዝን ቲኤቲፒ የተባለ ተቀጣጣይ ነገር እና ተቀጣጣዩን ነገር በርቀት ለማፈንዳት የሚረዳ ቁስ ነው ተብሏል።
ዲፕሎማቱ ጥንዶቹ ከፈረንሳይ መዲና ፓሪስ በቅርብ ርቀት ላይ በተካሄደው ጸረ የኢራን መንግሥት ሰልፍ ላይ ቦምቡን እንዲያፈነዱት ትዕዛዝ ሰጥቷል ይላል ፖሊስ። የተቃውሞ ሰልፉን ያዘጋጀው ፓርቲ የኢራን ኢስላማዊ ሪፓብሊክ መንግሥት ከስልጣን እንዲወገድ የሚሰራ ፓርቲ ነው።
ኤንሲአርአይ የተባለው ፓርቲ በኢራን መንግሥት “ሽብርተኛ ድርጅት” ተብሎ ተፈርጇል። ሶስቱ ግለሰቦች በላክሰመበርንግ ምግብ ቤት ውስጥ ከተገናኙ ከሁለት ቀናት ክትትል በኋላ በአውሮፓ የደህንነት ሰራተኞች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተነግሯል።
ተጠርጣሪዎቹም የሽብር ጥቃት በማሴር እና ዝግጅት በማድረግ በሚል የሽብር ወንጀል እንደሚጠየቁ ተጠቁሟል። ፈረንሳይ በበኩሏ የሽብር ጥቃቱን ለማድረስ የኢራን የደህንነት ሚንስቴር ከግለሰቦቹ ጋር አብሮ አሲሯል ስትል ከሳለች።
ቤልጄም በበኩሏ አሚር ኤስ የተባለው ዜጋዋ በኢራን የደህንነት ሰዎች የተመለመለው እአአ 2012 ነበር። ከዚህ በተጨማሪም አሚር በጀርመን እና ኦስትሪያ ከዲፕሎማቱ አሳዲ ጋር ለበርካታ ጊዜ ተገናኝቷል።