ኮሮረናቫይረስ፡ ብዙ ተስፋ የተጣለበት የኦክስፎርድ ክትባት አስተማማኝነቱ 70 በመቶ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የበለጸገው የኮሮናቫይረስ ክትባት ሰዎችን 70 በመቶ ከቫይረሱ መጠበቅ ያስችላል ተባለ።
ይህ የክትባቱ ውጤት ይፋ የሆነው የክትባቱ ውጤታማነትን ለመፈተሽ የተካሄደው ጥናት ውጤት መታወቁን ተከትሎ ነው።
የኦክስፎርድ ክትባት አስተማማኝነቱ 70 በመቶ ነው መባሉ በባለሙያዎች ዘንድ የተለያየ ስሜትን ፈጥሯል።
ከዚህ ቀደም ይፋ የተደረጉት የፋይዘር እና ሞደርና ክትባቶች አስተማማኝነት 95 በመቶ መሆኑ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ የኦክስፎርድ ክትባት ከሁለቱ ክትባቶች አንጻር ዋጋው ርካሽ መሆኑ እንዲሁም ኦክስፎርድ ሰራሽ ክትባትን ማጓጓዝ እና ማከማቸት ከሁለቱ ክትባቶች አንጻር እጅግ ቀላል መሆኑ በመልካም ጎኑ ተጠቃሽ ሆኗል።
በዚህም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የኦክስፎርድ ክትባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል። የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አስቀድሞ 100 ሚሊዮን የኮሮናቫይረስ ክትባት ብልቃጦችን ለመግዛት ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጋር ውል አስሯል።
ይህ ማለት ለ50 ሚሊዮን ሰዎች የሚበቃ ነው። ሰዎች ክትባቱን በሶስት ሳምንት ልዩነት ሁለት ጊዜ ይወስዱታል ተብሏል። የዩኬ ጤና ጥበቃ ኃላፊ ማት ሃንኮክ ለቢቢሲ፤ "ይህ ወደ ተለመደ አይነት ሕይወት ለመመለስ አንድ እርምጃ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ነዋሪነታቸው በዩናይትድ ኪንግደም እና ብራዚል የሆኑ 20 ሺህ ሰዎች ላይ የኦክስፎርድ ክትባት ሙከራው ተከናውኗል። የክትባቱን ሙከራ በበላይነት እየመሩ የሚገኙት ፕሮፌሰር አንድሩ ፖላርድ በክትባቱ ውጤት እጅግ ደስተኞች ነን ሲሉ ለቢቢሰ ተናግረዋል።
ክትባቱ መቼ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል?
የዩናትድ ኪንግደም መንግሥት 4 ሚሊዮን ክትባቶች ተረክቧል።
96 ሚሊዮን ብልቃጦችን ደግሞ በቅርቡ ከአምራቹ ይቀበላል ተብሏል። ክትባቱ ግን የመድሃኒት ተቆጣጠሪዎችን ይሁንታ ሳያገኝ ለሰዎች አይሰጥም።
መድሃኒት ተቆጣጣሪዎች የክትባቱን አቅም ለመፈተሽ እና ተጓዳኝ የጤና ችግር እንደማያስከትል ለማረጋገጥ ቢያንስ ሳምንታት ያስፈልጋቸዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም ክትባቱን በቅድሚያ ከሚያገኙት መካከል እድሜያቸው የገፉ ሰዎች፣ የአረጋውያን መኖሪያ ውስጥ የሚኖሩ አዛውንቶች እና የተቋማቱ ሰራተኞች፣ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም እድሜያቸው ከ80 ዓመት በላይ የሆናቸው አዛውንቶች ተጠቃሽ ናቸው።













