ኮሮናቫይረስ፡ አንጌላ መርክል ክትባቱ ለደሃ አገራት የሚደርስበት ሁኔታ አሳስቦኛል አሉ

የጀርመን መራሂተ መንግሥት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የጀርመን መራሂተ መንግሥት
ታትሟል

የጀርመን መራሂተ መንግስት የኮቪድ-19ኝን ክትባት እጅግ ደሀ የሚባሉት አገራት ላያገኙት ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው ገለጹ።

የአገራት መሪዎች ክትባቱን በአግባቡ ለማሰራጨት ቃል በገቡበት በጂ20 ስብሰባ ላይ ነው አንጌላ መርክል ይህንን ስጋታቸውን የገለጹት። ምንም እንኳን አገራት አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ ቃል ቢገቡም መርከል ግን አካሄዱ ፈጣን አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል።

''ለድሃ አገራት ክትባቱን ለማድረስ የሚደረገው ድርድር መቼ እንደሚጀመረ ከጋቪ ጋር አሁኑኑ እንነጋገራለን። ምክንያቱም እስካሁን በጉዳዩ ላይ ይህ ነው የሚባል ነገር እንዳልተሰራ ነው የማስበው፤ ይህ ጉዳይ ደግሞ ያሳስበኛል'' ብለዋል መራሂተ መንግሥቷ።

አንጌላ መርክል ይህንን ያሉት አሜሪካውያን በሚቀጥሉት 20 ቀናት ውስጥ ክትባቱን መከተብ እንደሚጀምሩ ከተገለጸ በኋላ ነው።

በሳኡዲ አረቢያ አረቢያ አዘጋጅነት በተካሄደው የጂ20 ስብሰባ ላይ በርካታ የአገራት መሪዎች ተገኝተዋል።

በመሪዎቹ ውይይት ላይም የሃብታም አገራት መሪዎች በወረርሽኙ ምክንያት ኢኮኖሚያቸው የደቀቀ አገራትን ለመርዳትና ክትባቱንም ለማዳረስ ቃል መግባታቸው ተገልጿል።

የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ከቻይናዋ ዉሀን ከተማ ተቀሰቀሰ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ወረርሽኙ በመላው ዓለም 60 ሚሊዮን ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን 1.4 ሚሊየን ሰዎች ደግሞ በዚሁ ቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።

ባሳለፍነው ሰኔ ወር የእንግሊዙ አስትራዜኒካ 2 ቢሊየን የኮሮናቫይረስ ክትባት መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አገራት ለማዳረስ ስምምነት ላይ መድረሱ የሚታወስ ነው።

አስትራዜኔካ ከሕንዱ ግዙፍ መድኃኒት አምራች ‹‹ሴሩም ኢንዲያ›› ጋር ያደረገው ስምምነት በአንድ ጊዜ አንድ ቢሊዮን የክትባት ብልቃጥ የማምረት ስምምነት ሲሆን ይህም በዋናነት ክትባቱን መግዛት ለማይችሉ አገራት የሚሆን ነው፡፡

በስብሰባው ላይ የሳኡዲ የገንዘብ ሚኒስትር ሞሐመድ አል ጃዳን እንደገለጹት አገራቱ የትኛውንም የዓለማችንን አገር ላለመተው ቃል መግባታቸውንና ''አንዲት አገር ወደኋላ ከቀረች ሁላችንም ወደኋላ ቀረን ማለት ነው'' የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው የጂ20 አገራት መሪዎች ድሃ አገራትን የመደፍ ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉና የክትባት ብልቃጦችን በድጋፍ መልክ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።