ትራምፕ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን እያባረሩ ነው

ታትሟል

ትራምፕ በምርጫው በለስ ሳይቀናቸው መቅረቱን ተከትሎ ባለሥልጣናትን ማባረር ሥራዬ ብለው ተያይዘውታል።

ትናንት የአገሪቱ የበይነ መረብ ደኅንነትና የደኅንነት መዋቅር ኤጀንሲ (Cisa) ኃላፊ የሆኑትን ክሪስቶፎር ክሬብስን ድንገት ከሥራ አግደዋል።

ሚስተር ክሪስቶፈር ከሥራ መባረራቸውን ያወቁትም በትራምፕ የትዊተር ሰሌዳ ላይ የተጻፈውን አንብበው ነው።

የሲሳ ኃላፊ ሚስተር ክሪስቶፈር ከሥራ ለመባረር ያበቃቸው ከምርጫ መጭበርበር ጋር በተያያዘ ከትራምፕ ጋር የሚቃረን አስተያየት በመስጠታቸው ነው ተብሏል።

ዶናልድ ትራምፕ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚሉበት ሰዓት እኚህ ባለሥልጣን ግን እንደዚህኛው ምርጫ የተዋጣለትና ደኅንነቱ የተጠበቀ ምርጫ የለም ሲሉ ነበር። ይህም ፕሬዝዳንቱን አበሳጭቷል።

የሲሳ ኃላፊ ክሪስቶፈር ከምርጫ ጋር በተያያዘ የበይነ መረብ ደኅንነት ከፍተኛ ኃላፊም ነበሩ።

ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ከፍተኛ የአሜሪካ ኃላፊዎች ይህ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በታሪክ እጅግ ደኅንነቱ የተጠበቀና ተአማኒው ነው ማለታቸው ትራምፕን ክፉኛ እያስቆጣና እያበሳጨ ይገኛል።

ባለፈው ሳምንትም በተመሳሳይ የመከላከያ ሚኒስትሩ ማርክ ኤስፐር ባልተጠበቀ ሁኔታ በትራምፕ ከሥልጣናቸው ተነስተዋል።

ሰውየው የተባረሩት ለትራምፕ ታማኝ ስለመሆናቸው በፕሬዝዳንቱና የቅርብ ባለሟሎቻቸው ዘንድ ጥርጣሬ በመፈጠሩ ነው።

አሁን ዶናልድ ትራምፕ ከዋይት ሐውስ እስኪወጡ ድረስ ሌሎች የአገሪቱን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ከሥራ ያባርራሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

የዋይት ሐውስ ውስጥ አዋቂዎች እንደሚገምቱት በቀጣይነት የሲአይኤ አለቃ ጊና ሀስፕል እና የኤፍቢአይ አለቃ ክሪስቶፎር ሬይ ከሰሞኑ ከሥልጣን ሊነሱ የሚችሉበት ዕድል አለ።

ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን የሚያባርሩበት መንገድ በአሜሪካ ታሪክ ያልተለመደ ነው።

ዋይት ሐውስ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በማባረር እንደ ትራምፕ ዘመን የታመሰበት ጊዜ የለም ይላሉ ተንታኞች።

የተባረሩት ባለሥልጣናትም መነሳታቸወን የሚረዱት ድንገት ከፕሬዝዳንቱ የትዊተር ሰሌዳ ላይ እንጂ መደበኛ ሂደትን ተከትሎ አይደለም።

የበይነ መረብና ደኅንነት ኤጀንሲው (ሲሳ) አለቃ ሚስተር ክርስቶፈር ክሬብስም እንደ ሌሎች የተባረሩ ባለሥልናት ሁሉ ከኃላፊነት መነሳታቸውን ያወቁት በድንገት ነው።

ሮይተርስ ወዳጃቸውን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ክሪስቶፈር ማክሰኞ ዕለት የትራምፕን ትዊት ሰሌዳ ሲያዩ ተገርመዋል።

የቀድሞው የማይክሮሶፍት ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት እኚህ ባለሥልጣን መባረራቸው ግን ብዙም አልጸጸታቸውም ተብሏል።

ሲሳ የተሰኘውን የበይነ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ከተቋቋመበት ከ2016 ጀምሮ የመሩት እኚሁ ባለሥልጣን ነበሩ።

ሲሳ የተቋቋመው የሩሲያ በ2016ቱ የአሜሪካ ምርጫ እጇን አስገብታለች መባሉን ተከትሎ ነው።

ሲሳ የሥራ ተግባርና ኃላፊነቶች ከጠላት አገር የሚነሱ የበይነ መረብ ደኅንነት ሥጋቶችን መመከት፣ በምርጫ ወቅት ደግሞ ሲስተምን ከባዕዳዊ ጥቃት መጠበቅና መቆጣጠር ነው።

ከምርጫ ጋር በተያያዘ ደግሞ ሲሳ ከግዛትና አካባቢ የምርጫ አስፈጻሚዎች ጋር በጥምረት የምርጫ ቆጠራ ሲስተምን በማሳለጥ፣ ደኅንነት በማስጠበቅ ኃላፊነቱን የሚወጣ መንግሥታዊ ተቋም ነው።

ትራምፕ የዚህ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ላይ ቂም የቋጠሩት ተቋሙ "ሐሜት ተቆጣጣሪ" የሚባል ድረገጽ ከከፈተ በኋላ ነው።

ይህ ድረ ገጽ የተጭበረበሩና ተጨባጭነት የሌላቸው በሬ ወለደ መረጃዎችን የሚያጋልጥ ሆኖ ቆይቷል።

ድረ ገጹ ከምርጫው ጋር በተያያዘ የትራምፕ ደጋፊዎች የሚያራግቧቸውን አሉባልታዎች እያደነ ማጋለጥ መጀመሩ ዶናልድ ትራምፕን ሳያበሳጭ አልቀረም።