ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
'በርሜል ሙሉ ገንዘብ ተገኘ የተባለው ሐሰት ነው' - አ/አ ፖሊስ
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአራዳ ክፍለ ከተማ በልመና በሚተዳደሩ አንዲት ግለሰብ ቤት ውስጥ ከ45 ሺህ በላይ ብር ማግኘቱን ሲያረጋግጥ፤ በርሜል ሙሉ ገንዘብ ተገኘ የሚለውን ዘገባ ሐሰት ሲል አስተባብሏል።
በክፍል ከተማው በተለምዶ አትክልት ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በልመና የሚተዳደሩት ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው ገንዘቡ የተገኘው።
ኮሚሽኑ ግለሰቧ ረዳትም ሆነ ልጅ በአጠገባቸው የሌላቸው የአእምሮ ህመም ያለባቸው ናቸው ያለ ሲሆን፤ ገንዘቡ የተገኘው በተለያዩ ፌስታሎች ነው ይላል ኮሚሽኑ በፌስቡክ ገፁ ያሰፈረው ዜና።
የአካባቢው ነዋሪዎች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ መሰረት ፖሊስ ሁኔታውን ለማረጋገጥ ወደ ስፍራው በማምራት ገንዘቡን እንዳገኘ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።
"በቦታው ላይ በተደረገው የማረጋገጥ ሥራ በግለሰቧ መኖሪያ ቤት ውስጥ በርካታ የተቋጠሩ ፌስታሎች እና ሌሎች ቆሻሻ ዕቃዎች ተከማችተው የተቀመጡ ሲሆን ከተቋጠሩት ፌስታሎች መካከል ገንዘብ ያለባቸው" ይላል የኮሚሽኑ ገለፃ።
በልብስ መዘፍዘፊያ ፕላስቲክ የተወሰነ ብር እንደተገኘ የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከአካባቢው ነዋሪዎች ታዛቢዎችን በመጨመር ፖሊስ እና የወረዳው አስተዳደር ባደረጉት ቆጠራ የተገኘው ገንዘብ 45 ሺህ 858 ብር መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ፖሊስ ኮሚሽኑ ጨምሮ እንደገለጸው ከተገኘው ገንዘብ ውስጥ አንድ ሺህ ብር ግለሰቧ ለዕለት ወጪያቸው እንዲጠቀሙበት የተሰጣቸው ሲሆን፤ ቀሪው ብር ደግሞ በግለሰቧ ስም የባንክ የሂሳብ ተከፍቶ ገቢ ተደርጎላቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በርሜል ሙሉ ገንዘብ ተከማችቶ ተገኘ በሚል በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች እየተላለፈ ያለው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታዉቋል።
ማክሰኞ ረፋዱ ላይ አራዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ኢንፎኔት ኮሌጅ አካባቢ አንድ በርሜል ገንዘብ ወድቆ ተገኝቷል ሲሉ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበው ነበር።
የተገኘው ገንዘብ የኢትዮጵያ ብር እና ዶላር እንደሆነና ገንዘቡን ማን እንደጣለው ያልተተረጋገጠ መሆኑን በመግለጽ የአካባቢው ፖሊስ በመኪና ጭኖ እንደወሰደውም ተዘግቦ ነበር።
ኮሚሽኑ ግን ይህ ዘገባ የተሳሳተ ነው ሲል አስተባብሏል።