የተፈጥሮ አደጋ፡ በጓቲማላው የመሬት መንሸራተት ቢያንስ 50 ሰዎች ሞቱ

ታትሟል

በጓቲማላ የጣለውን አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ተከትሎ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ቢያንስ 50 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተዘግቧል።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አሌሃንድሮ ጂያማቴ እንዳሉት ካጋጠመው የሰዎች ሞት መካከል ግማሽ የሚሆኑት የተከሰቱት በአንዲት ከተማ ውስጥ ሲሆን አንድ ጉብታ በመደርመሱና 20 መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት በማድረሱ ነው።

ቤቶቹ በእርጥብ አፈር ተቀብረው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ አክለውም ለአንድ ወራት ያክል ሊዘንብ የሚገባው የውሃ መጠን በግማሽ ቀን ውስጥ በመውረዱ አደጋው ሊያጋጥም እንደቻለ አስረድተዋል።

በአሁኑ ሰአት ከባዱ ዝናብ አሁንም ሙሉ በሙሉ ያላባራ ሲሆን የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም በዚህ ምክንያት እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ነብስ የማዳን ስራቸውን እንዳያከናውኑ አግዷቸዋል።

''በአሁኑ ሰአት ሌላ ምንም አማራጭ ስለሌለን ጉዳት ወደደረሰባቸው አካባቢዎች በእግር እየገባን ነው'' ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

አውሎ ነፋስ የቀላቀለው ዝናብ ኒካራጓ ሲደርስ በሰአት 225 ኪሎሜትር ይጓዝ የነበረ ሲሆን በአገሪቱ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ወደ ጎረቤት አገራት ሁንዱራስ እና ጉዋቲማላ ማቅናቱ ተዘግቧል።

እስካሁንም በማዕከላዊ የአሜሪካ አገራት 70 ሰዎች በዚሁ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።

ኒካራጉዋ ውስጥ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን በአሁኑ ሰአት በጊዜያዊ ማቆያዎች ውስጥ ነው የሚገኙት።

በአገሪቱ ሰሜናዊ ዳርቻዎች አካባቢ ደግሞ በመሬት መንሸራተት ሁለት ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

በሆንዱራስ ደግሞ አንዲት የ13 ዓመት ታዳጊ በሳን ፔድሮ ከተማ የመኖሪያ ቤታቸው ግድግዳ በተኛችበት ወቅት ተደርምሶባት ሕይወቷ ማለፉ ተዘግቧል።

መንግሥት እስካሁን 500 የሚሆኑ ሆንዱራሳውያን ጎርፉን ፍራቻ ከተቀመጡባቸው የመኖሪያ ቤት ጣሪያዎች ላይ ማዳን መቻሉን የገለጸ ሲሆን የውሀው መጠን አሁንም ከፍ እያለ እንደሆነ ተገልጿል።