አሜሪካ፡ ሶስት ታሪካዊ አብያተ ክርስትያናትን ያቃጠለው 25 ዓመት ተፈረደበት

ሆልደን ማቲውስ

የፎቶው ባለመብት, @LAFIREMARSHAL

ታትሟል

በአሜሪካዋ ሉዊዚያና ግዛት ሶስት ታሪካዊ የጥቁር አሜሪካውያን አብያተ ክርስትያናትን ያቃጠለው ወጣት ነጭ አሜሪካዊ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የ25 ዓመት እስር ተፈረደበት።

'ሄቪ ሜታል' በመባል የሚታወቅ የሙዚቃ አይነት አቀንቃኝ የሆነው የ 23 ዓመቱ ሆልደን ማቲውስ ከእስሩ በተጨማሪ 2.7 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍልም በፍርድ ቤት ተበይኖበታል።

ሆልደን ማቲውስ አብያተ ክርስትያናቱን ያቃጠለው ታዋቂነቱን ለመጨመር እንደሆነ ገልጿል።

ብይኑን ያስተላለፉት የፍርድ ቤቱ ዳኛ የግለሰቡ ተግባር ዘረኝነት ላይ መሰረት ያደረገ እንዳልሆነ በመግለጽ አብያተ ክርስትያናቱን ማቃጠሉ ግን በአሜሪካ የነበረውን የጨለማ ዘመን ያስታወሰ ነው ብለዋል።

በቀድሞው ዘመን በነጭ የበላይነት የሚያምኑ አሜሪካውያን የጥቁሮችን አብያተክርስትያናት ማቃጠል የተለመደ ነገር ነበር።

ጉዳት የደረሰባቸው 'ሴይንት ሜሪ ባፕቲስት ቸርች፣ ግሬተር ዩኒየን ባፕቲስት ቸርች እና ማውንት ፕሌዛንት ባፕቲስት አብያተ ክርስትያናት ከባለፈው መጋቢት እስከ ሚያዝያ ባሉት ጊዜያት ነበር የተቃጠሉት።

ሆልደን ማቲውስ በአካባቢው የሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ምክትል ኃላፊ ልጅ ሲሆን ሁለቱን ቤተክርስቲያኖች ካቃጠለ በኋላ ፎቶዎችና ተንቀሳቃሽ ምስል በፌስቡክ በኩል ለአድናቂዎቹ እንደለቀቀ አምኗል።

ምንም እንኳን በሁሉም አብያትክርስቲያናት ላይ ቃጠሎው ጉዳት ቢያደርስም በሰው ላይ ግን የደረሰ ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም። ምክንያቱ ደግሞ ወጣቱ ቃጠሎውን ያደረሰው በሌሊት ስለነበረ ነው።

ዳኛው ወንጀሉ በጥላቻ የተፈጸመ አይደለም ያሉ ሲሆን ባደረሰው ጉዳት ግን ወንጀለኛ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል።