ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ነጋዴዎች በምርጫ ምክንያት ሁከት ይፈጠራል የሚል ስጋት ገብቷቸዋል
የአሜሪካን ምርጫ ተከትሎ ሁከት ይፈጠራል በሚል ስጋት በአሜሪካ ያሉ የሱቅ ባለቤቶች መስኮቶቻቸውን እና በሮቻቸውን አጠናክረው መዝጋት ጀምረዋል፡፡
ጥንቃቄው የተጀመረው የጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ እጅ መሞትን ተከትሎ በተቀሰቀሱ ሰልፎች ላይ በርካታ የንግድ ድርጅቶች ከተዘረፉ ከጥቂት ወራት በኋላ ነው፡፡
ትልልቅ ኩባንያዎችን ጨምሮ ብዙ የንግድ ተቋማት ጥንቃቄ ከሚወስዱት መካከል ይገኙበታል፡፡
ብሔራዊ ቅድመ ምርጫ ድምጾች እንደሚያመለክቱት ጆ ባይደን ተቀናቃኛቸው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን እየመሩ ነው፡፡
ውጤቱን ሊወስኑ በሚችሉ ጥቂት ግዛቶች ግን ባይደን በጠባብ ውጤት ነው የሚመሩት፡፡
በየትኞቹ ድምጾች ይቆጠራሉ በሚለው ላይ የሕግ ሙግቶች በብዙ ግዛቶች ቀደም ተብሎ ተጀምሯል፡፡
በ2000 የፍሎሪዳ ውጤት በድጋሚ ይቆጠር መባሉ የምርጫው ውጤት ላይ እርግጠኛ አለመሆንን በመፍጠሩ የፋይናንስ ገበያዎች ወደ 5% ገደማ ማጣታቸውን የገለፁት የዋሽንግተን የፖሊሲ ዋና ስትራቴጂስት ብሪያን ጋርድነር ናቸው፡፡
የባይደንን ድል የገመቱት ጋርድነር፤ የውጤት እና የሁከት ርዕሶች መነሳታቸው በዚህ ወቅት የፋይናንሱ ዘርፍ ይበልጥ መውደቅን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ዎልማርት ባለፈው ሳምንት በሺዎች በሚቆጠሩ መደብሮቹ ጠመንጃዎችን እና ጥይቶችን ለጊዜው አንደማይሸጥ “ህዝባዊ አመፅን” በምክንያትነት አቅርቦ ገልጿል፡፡
ከአንድ ቀን በኋላ ግን ውሳኔውን ቀልብሶታል፡፡
ሁከት ይኖራል በሚል የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ዜጎቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስጠንቅቋል፡፡
ከ96 ሚሊዮን የሚበልጡ አሜሪካውያን ቀደም ብለው ድምፃቸውን የሰጡ ሲሆን፤ አገሪቱ በአንድ ምዕተ ዓመት ውስጥ ከፍተኛ ህዝብ የተሳተፈበት ምርጫ በማስመዝገብ ሂደት ላይ ናት።