ሥራቸው ለጥቃት ያጋለጣቸው የካሽሚር ጋዜጠኞች

ታትሟል

ሕንድ በምታስተዳድረው ካሽሚር ጋዜጠኝነት ለአደጋ የሚያጋልጥ ሙያ ሆኗል። በተለይም መንግሥት ባለፈው ነሐሴ ካሽሚርን ከልዩ ግዛትነት ካስወጣት በኋላ ነገሮች ተባብሰዋል።

ባለፈው ሳምንት የሕንድ ጸረ ሙስና ተቋም ግሬተር ካሽሚር የተባለውን መጽሔት ቢሮ እና የኤኤፍፒ ጋዜጠኛ ፓሪቫዝ ቡካሪ ቤትን በርብሮ ነበር።

የተራድኦ ድርጅቶችና የመብት ተሟጋቾች ቤቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ ዘጠኝ መኖሪያዎች ተፈትሸዋል። ብርበራው የተካሄደው እነዚህ ተቋሞች “አስገንጣዮችን ለመደገፍ ከውጪ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገላቸው አስተማማኝ መረጃ ስለተገኘ ነው” ተብሏል።

ተቺዎች ግን በዚህ አይስማሙም። ፍተሻው የንግግር ነጻነትን ይጋፋል ይላሉ። ቢያንስ 18 ጋዜጠኞች በፖሊስ ተጠይቀዋል ብዙዎችም ተንገላተዋል። ከጋዜጠኞቹ አምስቱ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አውቂብ ጃቪድ

የ28 ዓመቱ ጋዜጠኛ አውቂብ በስሪንጋር የመረጃ ደህንነት ተጠርቶ ነበር። ፖሊሶች በቅርቡ የታተመን ዜና ርዕስ እንዲቀይር ጠይቀውታል።

አርቲክል 14 በተባለ ድረ ገጽ ላይ የካሽሚር የትዊተር ተጠቃሚዎች በፖሊስ ከተጠሩ በኋላ ዝምታ መምረጣቸውን የሚገልጽ ጽሑፍ ነበር የጻፈው።

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 370 ካሽሚር የተሰጣትን ልዩ ግዛትነት የሕንድ መንግሥት ሰርዟል። የካሽሚር ነዋሪዎች ይህንን ይቃወማሉ።

ጋዜጠኛው ፖሊስ ጣቢያ ሳለ ጭምብል ያደረገ ፖሊስ በጥፊ እንደመታው ይናገራል።

ፖሊስ የጋዜጠኛው ዘገባ “አሳሳችና ሐሰተኛ ነው” ይላል።

አውቂብ የፖሊስ ጫና ሲበረታበት አርታኢው ጋር ደውሎ የዜናው ርዕስ እንዲቀየር አድርጓል። በዘገባው ውስጥ የፖሊስ ጣቢያው ፎቶ በመካተቱም ድረ ገጹ ይቅርታ ጠይቋል።

“ጋዜጠኞች ሲደበደቡና ሲንገላቱ ማንም ተጠያቂ ስለማይደረግ ድርጊቱ ይቀጥላል” ብሏል ጋዜጠኛው።

ፔሪዛ አሺቅ

ፖሊስ የ39 ዓመቱ ጋዜጠኛ ፔሪዛን በተመለከተ ቅሬታ ያቀረበው ግንቦት ላይ ነው።

መንግሥት የሁለት ታጣቂዎችን አስክሬን ቤተሰቦቻቸው ቆፍረው እንዲያወጡ መፍቀዱን የሚጠቁም ዘገባ ጽፎ ነበር።

ታጣቂዎቹ የተገደሉት ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ሲታኮሱ ነበር። መንግሥት የቀብር ሥነ ሥርዓት ከተካሄደ ወረርሽኙን ያስፋፋል ብሎ አስክሬናቸውን ለቤተሰቦቻቸው አልሰጠም።

ከታጣቂዎቹ ቤተሰቦች አንዱ የሟችን አስክሬን ቆፍሮ እንዲወስድ እንደተፈቀደለት ለጋዜጠኛው ነግሮታል። መንግሥት ግን በጉዳዩ ላይ ምላሽ አልሰጠም።

ዜናው ሲወጣ ፖሊስ “ሐሰተኛ ነው” አለ።

ከዛም ዘ ሂንዱ የተባለው ሚዲያ ማረሚያ አወጣ። የታጣቂዎቹ ቤተሰቦች አስክሬኑ የተቀበረበትን ቦታ እንዲጎበኙ እንጂ አስክሬን ቆፍረው እንዲያወጡ አልተፈቀደም የሚል ጽሑፍ ታተመ።

ነገር ግን ጋዜጠኛው ሁለቴ ፖሊስ ጣቢያ ተጠርቷል። ማስፈራሪያም ደርሶታል።

“ፖሊሶች ሊጠይቁኝ ቢወስዱኝም ሊቀጡኝ የፈለጉ ይመስል ነበር” ብሏል ፔሪዛ።

አኑራዳ ባህሲን

የ52 ዓመቷ ጋዜጠኛ የምትሠራበት ካሽሚር ታይምስ የሲንጋር ግዛት ቅርንጫፍ ጥቅምት 19 ታሽጓል።

ያለምንም ማስጠንቀቂያ እንደታሸገ አኑራዳ ትናገራለች። ስለዚህም ከቤታቸው ለመሥራት ተገደዋል።

ፖሊስ ስለ ጉዳዩ ለቢቢሲ ማብራሪያ ለመስጠት አልፈቀደም።

ጉልድ ኦፍ ኢንድያ እንደሚለው፤ ይህ እርምጃ መገናኛ ብዙኃን ላይ ጫና ያሳድራል።

ጋዜጠኛዋ፤ በቀጠናው የመስመር ስልክን፣ ኢንተርኔት እና ማኅበራዊ ሚዲያ መታገዳቸውን በመቃወም አምና ፊርማ አሰባስባ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አስገብታ ነበር።

“ፍርድ ቤት ሄጄ በማግሥቱ ጋዜጣው ላይ ማስታወቂያ ያወጡ የነበሩ የመንግሥት ተቋሞች እንዲያቆሙ ተደረጉ” ትላለች።

ፋሀድ ሻህ

ዘ ካሽሚር ዋላ የተባለ ሳምንታኢ መጽሔት እና ድረ ገጽ መስራችና አርታኢ ነው።

የ30 ዓመቱ ጋዜጠኛ በታጣቂዎች እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እንደተደረገ ከዘገበ በኋላ ነበር በፖሊስ የተወሰደው።

በዘገባው መሠረት ግጭቱን ተከትሎ ወደ 15 ቤቶች ላይ ጉዳት ደርሷል።

ፖሊሶች ግን “ስማችንን አጥፍቷል” ብለው ከሰውታል።

“ተኩሱ ሲጀመር ሁሉም መገናኛዎች ተቋርጠዋል። ታዲያ እንዴት ፖሊስን ማግኘት እንችል ነበር?” ሲል ፋሀድ ይጠይቃል።

ፖሊሶች ለሁለተኛ ጊዜ ሲጠሩት “ሐሰተኛ ዜና በማሰራጨት እና ግጭት በማጫር” ወንጅለውታል።

ፋሀድ ፖሊስ ጣቢያ መወሰድ እና መንገላታት እየተለመደ መምጣቱን ይናገራል።

ማስራት ዛራ

የ26 ፎቶ ዓመቷ ጋዜጠኛ “አሁን የመናገር ድፍረቱ ያለው ሰው የለም። በፖሊሶች ምክንያት ሥራቸውን ያቋረጡ ብዙ ጋዜጠኞች አውቃለሁ” ትላለች።

ግንቦት ላይ ፎቶ በመለጠፍ ሕግ ተላልፈሻል ተብላ በፖሊስ ተወንጅላ ነበር።

የተወነጀልበት ፎቶ የተነሳው 2018 ላይ ነበር። ቀብር ላይ ቡርሀን ዋኒ የተባለ ታጣቂ ፎቶ ተይዞ ሲለቀስ ያሳያል።

የ22 ዓመቱ ቡርሀን ሞት ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቶ ነበር።

የሕንድን አገዛዝ የሚቃወሙ የካሽሚር ነዋሪዎች፤ ከፖሊስ ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የተገደለው ቡሀርንን ሰማዕት ይሉታል።

እስካሁን ጋዜጠኛዋ ባትታሰርም ክሷ አልተዘጋም።

“በማንኛው ሰዓት ሊያስሩኝ እንሚችሉ ይሰማኛል። እኔን በማሰር ሌሎች ጋዜጠኞችን ማስፈራራት ይፈልጋሉ” ስትል ስጋቷን ትገልጻለች።