በፈረንሳይ ጥቃት ያደረሰው ከሰሜን አፍሪካ በስደተኞች ጀልባ አውሮፓ የገባ ነው ተባለ

ፈረንሳይ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

ትናንት በፈረንሳይ ኒስ ከተማ ሦስት ግለሰቦች በስለት ወግቶ የገደለው ቱኒዚያዊ ወጣት አውሮፓ የደረሰው ከጥቂት ቀናት በፊት ነው ተባለ።

የ21 ዓመቱ ተጠርጣሪ ከሰሜን አፍሪካ በስደተኞች ጀልባ ጣሊያን ከደረሰ በኋላ የጣሊያን ቀይ መስቀል ሲደርስ የስደተኛ ወረቀት ተሰጥቶታል ተብሏል።

ፖሊስ ተጠርጣሪው ብራሂም አውሳውሲ ጥቃቱ በተፈጸመበት ስፍራ ከፖሊስ በተተኮስበት ጥይት ተመትቶ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል ብሏል።

በጥቃቱ ሦስት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ሁለቱ የተገደሉት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው።

ፖሊስ በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል አንዷ የ60 ዓመት ሴት አንገቷ በስለት ተቀልታ ነው የተገደለችው ብሏል። ሌላኛው ሟች የ55 ዓመት ሰው ደግሞ ጉሮሯቸው በስለት ተወግቶ ተገድለዋል።

ሌላኛው በጥታቱ የተገደለችው የ44 ዓመት ሴት ጥቃት አድራሹ በተደጋጋሚ በስልት ቢወጋትም ከስፍራው አምልጣ በአንድ ካፍቴሪያ ውስጥ ተሸሽጋ ነበር። ይሁን እንጂ በደረሰባት ጉዳት ሕይወቷ አልፏል።

የኒስ ከተማ ከንቲባ ክርስችን ኤስቶርሲ ጥቃት አድራሹ ጥቃቱን ሲጸም በተደጋጋሚ 'አላሁ አክበር' ይል ነበር ብለዋል። ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ጥቃቱን "እላማዊ የሽብር ጥቃት" ሲሉ ገልጸውታል።

ፕሬዝደንት ማክሮን በትምህርት ቤት እና በቤተ ክርስቲያን አቅራቢያዎች የሚሰማራ የፖሊስ ቁጥርን ከ3ሺህ ወደ 7ሺህ ከፍ እንደሚል አስታውቀዋል።

ፈረንሳይም ብሔራዊ ደህንነት ስጋቷን "ከፍተኛ ደረጃ" ወደሚለው ደረጃ ከፍ አድርጋለች።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተማዋ ውስጥ ጥቃቶች በተደጋጋሚ እየተሰነዘሩ ነው።

ከአራት ዓመታት በፊት የ31 ዓመት ቱኒዝያዊ በዓል ለማክበር የተሰበሰቡ ሰዎች ላይ በጭነት መኪና ጥቃት አድርሶ 86 ሰዎች ሞተዋል። ከቀናት በኋላ ጃክዊስ ሀሜል የተባሉ ቄስ ጸሎት እየመሩ ሳለ አንገታቸውን ተቀልተዋል።

በዚህ ወር መባቻ ላይ በሰሜን ምዕራብ ፓሪስ ሳሙኤል ፓቲ የተባለ የታሪክ መምህር በተመሳሳይ አንገቱን ተቀልቶ መገደሉ ይታወሳል። መምህሩ ከመገደሉ በፊት የነብዩ መሐመድን አወዛጋቢ የካርቱን ሥዕል ለተማሪዎቹ አሳይቶ ነበር።

ጥቃቱን ተከትሎ ፕሬዝደንት ማክሮን በፈረንሳይ እክራሪነትን ለመታገል ቃል መግባታቸውን ተከትሎ ከቱርክ እና ከሌሎች አገሮች መንግሥታት ጋር አለመግባባት ውስጥ ከቷቸዋል።

የቱርኩ ፕሬዘዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ኢማኑኤል ማክሮን "የጤና ሕክምና ያስፈልጋቸዋል" ማለታቸው ይታወሳል። ኤርዶዋን የፈረንሳይ ምርቶች ላይ ማዕቀብ እንዲጣልም ጠይቀዋል።

ይህንንም ተከትሎ በበርካታ የአረብ አገራት የፈረንሳይ ምርቶች ከመደብሮች መደርደሪያ ላይ ተነስተዋል።