በኒው ዚላንድ ሰዎች በፍቃዳቸው እንዲሞቱ የሚደነግግ ሕግ ሊወጣ ነው

የፎቶው ባለመብት, Matt Vickers
በኒው ዚላንድ በጠና የታመሙ ሰዎች በፍቃዳቸው እንዲሞቱ የሚደነግግ ሕግ ሊወጣ ነው።
ባለፈው ወር በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ 65.2% መራጮች የፍቃድ ሞትን ደግፈዋል።
ዩትኔዝያ ወይም የፈቃድ ሞት በጠና የታመሙ ወይም ከስድስት ወር በላይ እንደማይኖሩ የተነገራቸው ሰዎች በህክምና እርዳታ ሕይወታቸው እንዲያልፍ የሚደረግበት ሂደት ነው።
ሕጉ በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ወር ጸድቆ ይተገበራል ተብሎ ይጠበቃል።
ኒው ዚላንድ ሕጉን ካጸደቀች የፈቃድ ሞት ከሚተገበርባቸው ጥቂት አገሮች አንዷ ትሆናለች። ዩትኔዝያ ከተፈቀደባቸው አገሮች ኔዘርላንድ እና ካናዳ ይጠቀሳሉ።
ኒው ዚላንዳውያን ባለፈው ወር መሪያቸውን ሲመርጡ ስለ ፈቃድ ሞት እና ዕጸ ፋርስ ሕዝበ ውሳኔ አድርገዋል።
ዕጸ ፋርስን ለመዝናኛ መጠቀም ሕጋዊ እንዲሆን ድምጽ የሰጡት 46.1% ብቻ ሲሆኑ፤ 53.1% ተቃውመዋል።
የፈቃድ ሞትን ጠቅላይ ሚንስትር ጀሲንዳ አርደን እንዲሁም ተቀናቃኛቸው ጁዲት ኮሊንስም ይደግፉታል። ሕዝቡም ሕጋዊ ይሁን ብሎ እንደሚመርጥ ይጠበቅ ነበር።
ባለቤቱ የሞተችበት ማት ቪከርስ "ርህራሄ እና ደግነት አሸንፈዋል። በጠና የታመሙ ኒው ዚላንዳውያን ሕይወታቸውን ማሳለፍ ስለሚችሉ ደስ ብሎኛል" ሲል የተሰማውን ገልጿል።
ጠበቃ የነበረችው ባለቤቱ የአንጎል እጢ ሲገኝባት በፈቃዷ ለመሞት ክስ ብትመሠረትም ሳታሸንፍ በጠና ታማ ከአምስት ዓመታት በፊት ሞታለች።
"ባለቤቴ መሞት አትሻም ነበር። ማንም ሰው መሞት አይፈልግም። ነገር ግን መኖር የምርጫ ጉዳይ ነው። ስቃይ እየበረታ ሲሄድ መሞት አንዱ ምርጫ መሆን አለበት" ብሏል።
አንድ ሰው በፈቃዱ ለመሞት በጠና የታመመ ወይም ከስድስት ወር በላይ እንደማይኖር የተረጋገጠ መሆን አለበት።
ሰውነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ እንደሄደና ውሳኔው ላይ ለመድረስ በቂ መረጃ እንዳለው ማረጋገጥም ተገቢ ነው።
ሂደቱ የሚመራው በዶክተር ወይም በነርስ ነው።
አንድ ሰው እድሜው ስለገፋ፣ የአእምሮ ህመም ስላለበት ወይም የአካል ጉዳት ስላለበት የፍቃድ ሞት ሕግን መተግበር አይችልም።
ሕጉን የሚቃወሙ ሰዎች "እንድንኖር እንጂ እንድንሞት አትርዱን" ሲሉ ምክር ቤት ሄደው ተቃውሞ አሰምተዋል።
ሕጉ ለማኅበረሰቡ አስጊ እንደሆነ እና ራስን ማጥፋትን ለመግታት ከወጣ መርህ ጋር እንደሚቃረን ይናገራሉ።
ሌላው መከራከሪያ ነጥብ በጠና የታመሙ ሰዎች የቤተሰብ ሸክም ላለመሆን ብለው በፈቃዳቸው ሊሞቱ ይችላሉ የሚለው ነው።
ዩትኔዝያን አጥብቆ ሲተች የነበረ ቡድን "የኒው ዚላንድ ዜጎች የተሳሳተ ሕግ እንዲጸድቅ ድምጽ በመስጠታቸው አዝነናል" ሲል መግለጫ አውጥቷል።
የፈቃድ ሞትን ሕጋዊ ያደረጉ አገሮች የኒው ዚላንድን ሕዝበ ውሳኔ በቅርበት ሲከታተሉ ነበር። ከነዚህ መካከል ቤልጄም፣ ካናዳ፣ ኮሎምቢያ፣ ሉግዘምበርግ እና ኔዘርላንድስ ይጠቀሳሉ።
በኔዘርላንድስ በህክምና ታግዞ ራስን ማጥፋት ይቻላል።
በአሜሪካ ያሉ ብዙ ግዛቶች እና የአውስትራሊያዋ ቪክቶሪያ በህክምና የታገዘ ሞትን ፈቅደዋል።












