የሩሲያ መረጃ መንታፊዎች የቶኪዮ ኦሎምፒክን ኢላማ አድርገው ነበር ተባለ

የቶኪዮ ኦሎምፒክስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የሩሲያ መረጃ መንታፊዎች የቶኪዮ ኦሎምፒክን ኢላማ ማድረጋቸውን የዩናይትድ ኪንግደም ባለስልጣናት አስታወቁ።

በዚህ አመት በጃፓኗ መዲና ቶኪዮ ሊካሄድ ተይዞ የነበረውንም ኦሎምፒክም የማደናቀፍ እቅድ ነበራቸው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ቢሮ እንዳለው የሩሲያ ወታደራዊ ደህነንት አስተዳደር ጂአርዩ በኦሎምፒክ ተሳታፊ ድርጅቶችና ባለስልጣናቶች ላይ የሳይበር ጥቃቶችን አድርሰዋል ብለዋል።

የተባሉት ጥቃቶች የተፈፀሙት የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በኮሮናቫይረስ ከመራዘሙ በፊት መሆኑም ተገልጿል።

የደረሰው የሳይበር ጥቃት ምን አይነት ወይም በምን ያህል ደረጃም እንደሆነ አልተገለፀም።

በተያያዘ ዜናም የአሜሪካው የፍትህ ዲፓርትመንት ስድስት የሩሲያ የደህንነት ሰራተኞችን የሩሲያን ጥቅም ለማስከበር በሚል የሳይበር ጥቃት አድርሰዋል በሚል ክስ መስርቷል።

ቡድኑ የ2018ቱን የክረምት ኦሎምፒክስ፣ የ2017ቱን የፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ለማደናቀፍና የዩክሬን ሃይል ማመንጫን ከጥቅም ውጭ ለማድረግ አሲረዋል እንዲሁም ሞክረዋል ይላል የአቃቤ ህግ ክስ።

"የሳይበር አቅሟን ኃላፊነት በጎደለው ወይም ለተንኮል ለመጠቀም በከፍተኛ ሁኔታ እንደ ሩሲያ ያሳደገ የለም" በማለትም የጠቅላይ አቃቤ ህግ ረዳት ጆን ዴሜሬስ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተናግረዋል።

ቡድኑም ያደረሰው ውድመትም ከፍተኛ እንደሆነም አክለው አስረድተዋል።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ እንዳሉት ጥቃቱ የኦሎምፒክስ አዘጋጆችን፣ ገንዘብ ለጋሾችንና እቃ አቅራቢዎችን በሙሉ ኢላማ ያደረገ ነው ብለዋል።

"ይህንን ተግባር በከፍተኛ ሁኔታ እናወግዛለን። ዩኬ እንዲህ አይነት ተንኮል የተሞላባቸውን የሳይበር ጥቃቶችም እንዳይፈፀሙ ለመከላከልም ከአጋሮቿ ጋር ትሰራለች" በማለትም አስረድተዋል።

ከሁለት አመታት በፊት በደቡብ ኮሪያ ፒዮንግቻንግ የተካሄደው የዊንተር (ክረምት) ኦሎምፒክስን ጥቃት በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ቢሮ መረጃ ይፋ አድርጓል።