30 በመቶ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ጀምረዋል- የትምህርት ሚኒስቴር

የፎቶው ባለመብት, ullstein bild
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለወራት ተቋርጦ የነበረው ትምህርት በትናንትናው ዕለት፣ ጥቅምት 9፣ 2013 ዓ.ም በተለያዩ አካባቢዎች በከፊል ተጀምሯል።
የትምህርት ሚኒስትር በትናንትናው ዕለት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን በሰጠው መረጃ መሰረት በመላ አገሪቱ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያሟሉ 30 በመቶ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ጀምረዋል።
በአማራ ክልል የ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ትምህርት መጀመሩን የክልሉ የትምህር ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ዶ/ር ይልቃል ትምህርት ቤቶች ዝግጅታቸውን ከጨረሱ ጥቅምት 16፣ 2013 ዓ. ም. የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንደሚጀመር አስረድተዋል።
ዶ/ር ይልቃል በመንግሥት የተሰራጩ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎች በአብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች የደረሱ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ለተማሪዎች አለመሰራጨታቸውን አስረድተዋል።
እነዚህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎች ያልተከፋፈሉባቸው ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች ወላጆቻቸው ባዘጋጁላቸው ጭምብል እየተጠቀሙ ዛሬ ና ነገ (ጥቅምት 11 እና 12) እንደሚከፋፈሉ አክለዋል።
ተማሪዎች ርቀታቸውን እንዲጠብቁም በአንድ መቀመጫ ላይ አንድ ተማሪ ብቻ እንዲቀመጥ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
የትምህረት ቢሮ ኃላፊዎች ተዘዋውረው በጎበኟቸው ስፍራዎች ይህንን ማስተዋላቸውን የሚናገሩት ኃላፊው ውሃ ባለባቸው አካባቢዎችም በትምህርት ቤቶች የውሃ አቅርቦት መኖሩን ይናገራሉ።
ተማሪዎች በዚህ ሳምንት ረቡዕና ሐሙስ ተማሪዎቻቸው ሙሉ ሙሉ ይመጣሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
ዶ/ር ይልቃል ዝግጅታቸውን ከጨረሱ ጥቅምት 16፣ 2013 ዓ. ም. የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንደሚጀመር ጠቁመዋል።
የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ገብረመስቀል ካህሳይ የ12ኛ ክፍል ትምህርት መጀመሩን እና ሌሎች ክፍሎችም ቀስ በቀስ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።
በትግራይ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና የሚያስፈትኑ 98 ትምህርት ቤቶች ትምህርት መጀመራቸውን የተናገሩት ኃላፊው በአንድ ክፍል ውስጥ 25 ተማሪዎች ብቻ እንዲማሩ መደረጉን ተናግረዋል።
ከትምህርት ሚኒስትር ለተማሪዎች እየተሰራጨ የሚገኘው የአፍና አፍንጫ ጭንብል እንዳልደረሳቸው የገለፁት ዶ/ር ገብረ መስቀል በአንፃሩ ትምዕት ለተማሪዎቹ ጭምብል በማቅረቡ መጀመራቸውን አክለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ተሰማ እንደገለጹልን ከወረዳና ከዛ በታች ባሉ ትምህርት ቤቶች ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ. ም ትምህርት ይጀመራል።
በዞን እና በከተማ አስተዳደር ያሉ ትምህርት ቤቶች ጥቅምት 30፣ በአዲስ አበባ ዙርያ ያሉት ከተሞች ትምርት ቤቶች ደግሞ ህዳር 15 ትምህርት ይጀምራሉ።
አቶ ኤፍሬም እንዳሉት፤ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የ8ኛ እና 12ኛ ክፍ ትምህርት ጥቅምት 16 እንዲጀመር ተወስኗል።
70 በመቶ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች የተቀመጠውን መስፈርት እንዳሟሉና ከትምህርት ሚኒስቴር 20 ሚሊዮን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ደርሷቸው እያከፋፈሉ መሆኑን ገልጸውልናል።
ትምህርት ሚኒስትር ባለፈው አንድ ሳምንት ውስጥ መሰራጨት ካለበት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሲሶ ያህሉ የተሰራጨ መሆኑንን ገልጾ፣ በቀጣይ ሳምንት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግሯል።
በዚህም በሀገሪቱ 50 ሚሊዮን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በየትምህርት ቤቶቹ ለማሰራጨት በታቀደው መሰረት እየተሠራ እንደሚገኝ ከአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀኖች አስታውቋል።



















