ኔዘርላንድ ከ12 አመት በታች ላሉ ታዳጊዎች የፈቃድ ሞትን ፈቀደች

ታትሟል

የኔዘርላንድ መንግሥት በማይድን በሽታ የተጠቁ ታዳጊዎች በፈቃድ ሞት ወይም በእንግሊዝኛው ዩቴኔዥያ (euthanasia) ተግባራዊ እንዲሆን ከሰሞኑ ፈቅዷል።

ታዳጊዎች ብሎ የጠቀሰው ከአስራ ሁለት አመት በታች የሆኑ ህፃናትን ሲሆን የጤና ሚኒስትሩ ሁጎ ደ ጆንጌም ይህ ህግ "መቋቋም በማይችሉትና ተስፋ በሌለው ሁኔታ የሚሰቃዩ" ህፃናትን ይታደጋቸዋል ብለዋል።

በኔዘርላንድ የፈቃድ ሞት ከአስራ ሁለት አመት በላይ ለሆኑ ታዳጊዎች የሚፈቀድ ሲሆን ይህም የሚፈፀመው ከህመምተኞችና የቤተሰቦች ፈቃድ ሲገኝ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ከአንድ አመት በታች ያሉ ህፃናትን በማይድን በሽታ ከተጠቁና በቤተሰብ ፈቃድ እስከተገኘ ድረስ እንዲሞቱ ይፈቀዳል።

በ አንድ አመትና በ12 አመት መካከል የሚገኙ በማይድን በሽታ እየተሰቃዩ የሚገኙ ታዳጊዎችን በተመለከተ ምንም ህግ ያልነበረ ሲሆን የአሁኑ ይፈቀድ የሚለው ጥያቄም አገሪቷን በሚመሯት አራት ጥምር ፓርቲዎች መካከል ከፍተኛ ውዝግብን ፈጥሯል።

ለወራትም ያህል የፓርላማ አባላቱ ሲነታረኩ ነበር። በተለይም ወግ አጥባቂው የክርስቲያን ፓርቲዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውመውታል።

ሆኖም በመጨረሻ የፈቃድ ሞት ይፈቀድ የሚለው አሸንፎ ህግ እንዲሆን ፀድቋል።

ከዚህ በኋላ ህጉን በተግባር ላይ ለማዋልም መመሪያዎች እንደሚወጡ የጤና ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የዚህ ህግ መቀየር አስፈላጊ መሆኑንም አንድ በባለሙያዎች የቀረበ ጥናት ማስረጃ ነው ይላሉ የጤና ሚኒስትሩ። በዚህ ጥናት መሰረት አዲሱ ህግ በአመት አስር የሚሆኑ በማይድን በሽታ የሚሰቃዩ ህፃናትን ህይወት ይቀይራል።

በስራ ላይ ያሉት ህጎች ሙሉ በሙሉ ይቀየራሉ ማለት እንዳልሆነ የጠቀሱት የጤና ሚኒስትሩ ነገር ግን ፍቃድ ያለው የፈቃድ ሞት ዶክተሮች ቢያከናውኑ ከመከሰስ ይከላከልላቸዋል።

በተሻሻለው ህግ መሰረትም ከ12 አመት በላይ ያሉ ታዳጎጊዎች የቤተሰብ ፈቃድ፣ ከፍተኛና መቋቋም የማይችሉት ህመምና ይህንን ተግባር ማከናወን የፈቀዱ ሁለት ዶክተሮች መስፈርቶች መሟላት አለባቸው።

እነዚህ ህጎችም በሚቀጥሉት ወራት ተግባራዊ ይሆናሉ።

የፈቃድ ሞት በኔዘርላንድ ህግ ሆኖ የፀደቀው በጎሮጎሳውያኑ 2002 ሲሆን ከወራት በኋላም ቤልጅየም በመፍቀድ ተከትላታለች።