ቱሪዝም፡ የታይላንድ ሆቴልን ያንቋሸሸው አሜሪካዊ አይታሰርም ተባለ

በታይላንድ የሚገኝ ሪዞርት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በታይላንድ የሚኖረው አሜሪካዊ በአንድ ሆቴል ላይ በጻፈው አሉታዊ አስተያየት ምክንያት ክስ እንማይመሰረትበትና እንደማይታሰር ተገለፀ።

ዌዝሊ ባርነስ ሲ ቪው ሪዞርት ስለተሰኘ መዝናኛ ስፍራ "ዘመናዊ ባርነት" በማለት በርካታ አሉታዊ አስተያየቶችን ጽፎ ነበር።

የታይላንድ መንግሥትም ግለሰቡን በቁጥጥር ስር በማዋል የአገሪቱን ስም ማጥፋት ሕጉን በመጥቀስ ከሶት ነበር።

አሁን ግን ፖሊስ ባርነስ እና ሪዞርቱ ስምምነት ላይ በመድረሳቸው መለቀቁን አስታውቋል።

ግለሰቡና ሪዞርቱ የደረሱበት ስምምነት ሆቴሉን እና የታይላንድ ቱሪዝም ባለስልጣንን ይቅርታ መጠየቅ ያካትታል።

በተጨማሪም መታሰሩን ለዘገቡ የውጭ አገር መገናኛ ብዙሃን፣ ቢቢሲን ጨምሮ፣ ደብዳቤ አንዲጽፍ ተነግሮታል።

በደብዳቤውም "በተደጋጋሚ የሲ ቪው ሪዞርትን ስም ሆን ብሎ የሚያጠለሽ . . . ውሸት የሆኑና እውነታ ላይ ያልተመሰረቱ አስተያየቶችን ጽፌያለሁ። እነዚህ አስተያየቶች በንዴትና ለመጉዳት ሆን ብሎ በማሰብ የጻፍኳቸው ናቸው" ሲል አስፍሯል።

የፈረንሳይ ዜና ወኪል እንደዘገበው ባርነስ "ከአሜሪካ ኤምባሲ ማብራሪያ ማምጣት አለበት" ማብራሪያው ግን ስለምን እንደሆነ የተገለፀ ነገር የለም።

ሆቴሉም ግለሰቡ እነዚህን ሁሉ ቅድመ ሁኔታዎች የሚያሟላ ከሆነ ክሱን እንደሚያነሳ አስታውቋል።

ባርነስ ከድርድሩ በፊት ለሮይተርስ "ይህንን ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መዝጋት እፈልጋለሁ" ብሏል።

በክሱ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ሁለት ዓመት በሚደርስ እስራት ይቀጣል።

ይህን ሁሉ ክስና ውዝግብ ያስነሳው ኮህ ቻንግ በምትባለው ደሴት ውስጥ የሚገኘው ሪዞርት ውስጥ ያረፈው ዌስሊ የራሴን መጠጥ ማስገባት አለብኝ በሚል ከሆቴሉ አስተዳደር ጋር እሰጣገባ በመግባቱ ነው።

ግለሰቡ የሆቴሉን ተስተናጋጆች እንደረበሸና መጠጥ የሚያስገባም ከሆነ ክፍያውን ፈፅም ቢባልም እምቢተኝነት ማሳየቱን ሆቴሉ ባወጣው መግለጫው አትቷል።

ሆቴሉን ለቅቆ ከወጣም በኋላ በተደጋጋሚ አሉታዊ ነገሮችን ስለሆቴሉ መፃፉንም ተከትሎ ሆቴሉም በስም ማጥፋት ወንጀል ከሶታል።

ግለሰቡም በቁጥጥር ስር ውሎም ለሁለት ምሽቶች በእስር ቤት ያሳለፈ ሲሆን በዋስም ተለቅቋል።

አሜሪካዊው ግለሰብ በስም ማጥፋት ክስ ወንጀል ጥፋተኛም ሆኖ ከተገኘ እስከ ሁለት ዓመት የሚቆይ እስር ይጠብቀዋል ተብሏል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ ሥራውን ያጣው ግለሰብ ጉዳዩ የበለጠ ከገፋም ሌላ ሥራ ለማግኘት እንደሚቸገር ለቢቢሲ ተናግሯል።