ፈረንሳይና ጣልያን ዝናብ በቀላቀለ ከፍተኛ አውሎ ንፋስ ተመቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የተወሰኑ የፈረንሳይና ጣልያን ግዛቶች በከፍተኛ አውሎንፋስ መመታቸውን ተከትሎ 25 ሰዎች ጠፍተዋል፤ ሁለት ሰዎች ሞተዋል።
አሌክስ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ አውሎ ንፋስ ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለ ሲሆን ግዛቶቹንም በጎርፍ አጥለቅልቋቸዋል።
በርካታ የምዕራብ ኒስ ግዛት ነዋሪዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ከንቲባው እስከሚያስታውሱት ድረስ እንዲህ አይነት የከፋ ጎርፍ ገጥሞም እንደማያውቅ ነው።
በሰሜናዊ ጣልያንም ጎርፉ መንገዶቹንና ድልድዮቹን ጠራርጎ የወሰዳቸው ሲሆን። ወንዞችም ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልተዋል።
በጎርፉ ጉዳት ህይወታቸውን ካጡት መካከል አንደኛው ኦስታ ሸለቆ አካባቢ የእሳት አደጋ ሰራተኛ ነው ተብሏል።
ሌላኛው ደግሞ በ30ዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ግለሰብና ከመኪናው ጋር በወንዙ ተጠራጎ የተወሰደ ነው።
በአገሪቷ ሰሜን ምዕራብ ግዛት አስራ ሰባት ሰዎች የጠፉ ሲሆን ከነዚህም መካከል ተራራ ወጪ አራት ጀርመናውያን እንደሚገኙበት ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
በጎርፉ ክፉኛ በተመታችው ፔድሞንት ግዛትም የበርካታ መንደሮች መንገዶች ተሰባብረዋል። ባለስልጣናቱም ሁኔታውን የከፋ ነው ብለውታል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የእርዳታ ሰራተኞች በነዚህ መንደሮች ተሰማርተውም እያገዙ ነው።
አውሎ ንፋሱ የሰሜናዊ ምዕራብ ሎምባርዴና ሊጉሪያ ግዛቶችንም መትቷቸዋል።
በነሃሴ ወር ክፉኛ በሆነ አውሎ ንፋስ ተመትታ የነበረችው የቬኒስ ከተማም ከዚህ ጎርፍ ተርፋለች ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
በፈረንሳይ ስምንት ሰዎችም ጠፍተዋል።
በሰሜናዊ ኒስና አዋሳኝ ዝቅ ባለ ስፍራ የሚገኙ መንደሮች መንገዶች በመሰባበራቸው ግንኙነትን አስቸጋሪ አድርጎታል።
የመንገድ ጉዞ የማይቻል በመሆኑም የኒስ ከንቲባ ቺስታን ኤስትሮሲ በሂሊኮፕተር የደረሱ ሲሆን ለፈረንሳይ የዜና ወኪል ቢኤፍኤም እንደተናገሩት "መንገዶቹ በሙሉ ተበላሽተዋል። 100 ቤቶችም በጎርፉ ተጠራርገዋል" ብለዋል።












