ፍርድ ቤቱ ከትዳር ውጪ የተወለደችው "የቤልጄም ልዕልት" ተብላ ትጠራ፤ ንብረትም ትውረስ አለ

ታትሟል

የቤልጄም ፍርድ ቤት የቀድሞ የቤልጄም ንጉስ ከትዳር ውጪ የወለዷት ሴት ሙሉ ንጉሳዊ መጠሪያ እንዲኖራት በየነ።

የ52 ዓመቷ አርቲስት ዴልፊን ቦይል የቀድሞ ንጉስ በትዳር ከወለዷቸው ልጆች እኩል ንጉሳዊ መብት እና መጠሪያ ይኖራታል።

በዚህም ፍርድ ቤቱ አርቲስት ዴልፊን ቦይል "የቤልጄም ልዕልት" ተብላ ትጠራ፤ ንብረትም ትውረስ ሲል ወስኗል።

ዴልፊን ቦይል፤ የቀድሞ ንጉስ አልበርት አባቷ መሆናቸውን እንዲያምኑ ለበርካታ አስርት ዓመታት ስትጠይቅ ቆይታ የቀድሞ ንጉስ አልበርት ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ አባቷ መሆናቸውን አምነው ተቀብለዋል።

የዴልፊን እናት ባሮነስ ሲቢል እንደምትለው አልበርት ሁለተኛ ንጉስ ተብለው ከመሾማቸው በፊት ለ18 ዓመታት የቆየ የፍቅር ግንኙነት ነበራቸው።

ንጉስ አልበር ከትዳር ውጪ ልጅ ስለመውለዳቸው ጭምጭምታ መሰማት የጀመረው በአውሮፓውያኑ 1999 ይፋዊ ያልሆነው የንጉሱ ሚስት ንግስት ፖዎላ ባዮግራፊ ከታተመ በኋላ ነበር።

በመጸሃፉ ላይ ንጉሱ ከሌላ ሴት ልጅ መውለዳቸው ሰፍሮ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2005 ደግሞ አርቲስት ዴልፊን ቦይል በአንድ ቃለመጠይቅ ላይ ንጉስ አልበርት ሁለተኛ ወላጅ አባቷ እንደሆኑ የገለጸች ሲሆን ንጉሱ ያለመከሰስ መብት ስለነበራቸው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ እንደማትችል ተናግራ ነበር።

ይሁን እንጂ እአአ 2013 ላይ ንጉስ አልበርት በጤና እክል ምክንያት ከንግስናቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ዴልፊን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዳዋለች።

"የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የአባት ፍቅርን አይተካም፤ ነገር ግን ፍትህ ማግኘት ሰላምን ይሰጣል'' ሲሉ ተደምጠዋል ጠበቃዋ ማርክ ኡይቴንዴል።

ከዚህ በኋላም ዴልፊን ቦይል እና ሁለት ልጆቿ የንጉሳዊ ቤተሰብ መጠሪያ ይኖራቸዋል።

በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረት አልበርት ሕይወታቸው ሲያልፍ ዴልፊን ቦይል ከሌሎች ሶስት ልጆቻቸው ጋር ሙሉ የውርስ መብት ይኖራታል።

በተጨማሪም ንጉስ አልበርት ሁለተኛ ዴልፊን ላለፉት ዓመታት ለፍርድ ቤት ያወጣችውን ወጪ ካሳ እንዲሆን 3.4 ሚሊየን ዩሮ እንዲከፍሉ በፍርድ ቤቱ ተበይኗል።

ንጉስ አልበርት ሁለተኛ ታላቅ ወንድማቸው በ1993 ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ነበር በድንገት ንጉስ የሆኑት። እስከ ሐምሌ 2013 ድረስ ደግሞ በንጉስነት የቆዩ ሲሆን ከጤና እክል ጋር በተያያዘ ከንግስናቸው ወርደዋል።

በአሁኑ ሰአትም ልጃቸው ፊሊፕ ንጉስ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ።

ንጉስ አልበርት ሁለተኛ በፍርድ ቤት አባትነታቸውን የሚያረጋግጥ የዘረ መል ምርመራ እንዲያደርጉ ቢበይንባቸውም አሻፈረኝ ማለታቸውን ተከትሎ በየቀኑ 5 ሺ ዩሮ እንዲከፍሉ ተፈርዶባቸው ነበር።

ባሳለፍነው ዓመት ጥር ወር ላይ የዘረ መል ምርመራ ውጤቱን ተከትሎ ዴልፊን ልጃቸው መሆኗን አምነው ተቀብለዋል።