ጃፓን ፡ በአየር መንገድ መንገደኞችን "ክቡራትና ክቡራን" ማለት ሊያበቃ ነው

የጃፓን አየር መንገድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አውሮፕላንም ሆነ ዘመናዊ አውቶብሶች ላይ ሲሳፈሩ ከሚተላለፉ መልዕክቶች ቀድሞ የሚሰሙት "ክቡራትና ክቡራን መንገደኞቻችን" የሚለውን ሐረግ ነው።

ቃሉ ተሳፋሪዎችን ለመጥራት የሚውል የአክብሮት ቃል ነው። ክቡራት ለሴቶች፤ ክቡራን ደግሞ ለወንዶች።

በተለያዩ አየር መንገዶችም ይህንን መስማት የተለመደ ነው።

ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ በጃፓን አየር መንገድ ከተሳፈሩ ግን ይህንን ቃል አይሰሙትም ተብሏል።

በምትኩ ፆታን የሚያጣቅሰው ይህ መጠሪያ "መንገደኞቻችን" በሚል ወይም "ሁላችሁም መንገደኞችን" በሚል ፆታን የማይለይ የወል መጠሪያ እንደሚተካ 'ዘ ሚያኒቺ' የተሰኘው የጃፓን ጋዜጣ ዘግቧል።

ይህንን ተከትሎም የጃፓን አየር መንገድ ፆታን የማያመላክቱ ሰላምታዎችን በመቀበል ከዓለማችን ጥቂት አየር መንገዶች አንዱ ሆኗል።

ይሁን እንጂ ይህ ተግባራዊ የሚሆነው በእንግሊዝኛ ቋንቋ መልዕክት በሚተላለፍበት ጊዜ ብቻ እንደሆነ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ምክንያቱ ደግሞ በጃፓን ቋንቋ ቀድሞውኑ አገልግሎት ላይ የሚውለው ፆታን የማይጠቁም ቃል በመሆኑ እንደሆነ የዜና ወኪሉ ጨምሮ ገልጿል።

የአየር መንገዱ ውሳኔም በጃፓንኛ ላይ ያመጣው ለውጥ የለም።

በሂሮሺማ ሹዶ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ካዙያ ካዋጉቺ "ይህ በጣም ትንሽ ስምምነት ነው አብዛኛው ሰውም ምንም ግድ አይሰጠውም። በእንግሊዝኛ መልዕክቶቹ ላይ የተደረገውን ለውጥ ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ የጃፓን ቋንቋ ተናጋሪ መንገደኞች ሊረዱት ወይም ልብ ሊሉት አይችሉም" ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

አየር መንገዱ አገልግሎቱን ለሁሉም ምቹ ለማድረግ ባደረገው ጥረት ግን ሊደነቅ እንደሚገባ ፕሮፌሰሩ አክለዋል።

"ትላልቅ ድርጅቶች እንዲህ ዓይነት ልምድ መጀመራቸው ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም ሌሎች መካከለኛና አነስተኛ ድርጅቶችም እነርሱን የመከተል አዝማሚያ አላቸው" ብለዋል ፕሮፌሰሩ።

ኤር ካናዳ እና ኢዚጀት ፆታን የማያመላክቱ ሰላምታዎችን መጠቀም የጀመሩት ባለፈው ዓመት ነበር።

አየር መንገዱ ለሮይተርስ በሰጠው መግለጫው፤ ምቹ አካባቢን መፍጠርና ሁሉንም ሰው በአክብሮት መንከባከብ እንደሚፈልግ ተናግሯል።

"በፆታ፣ በፆታ ምንነት ወይም ሌሎች የግል ባህሪዎችን መሰረት ያደረገ መገለል ላለመፈፀም በትኩረት እንሰራለን" ሲሉም የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ ማርክ ሞሪሞቶ ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።

በጃፓን የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ በሕግ የተፈቀደ አይደለም። ነገር ግን አንዳንድ የዳሰሳ ጥናቶች ጠንካራ ድጋፍ እንዳለው እንደሚያመለክቱ ተግልጿል።