መንገደኛዋን ከመጸዳጃ ቤት ለማውጣት ሲባል አውሮፕላኑ ለማረፍ ተገደደ

የዩናይትድ አየር መንገድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዩናይትድ አየር መንገድ አውሮፕላን የሆነው የበረራ ቁጥር 1554 የመፀዳጃ ቤቱ በር አልከፈት በማለቱ ምክንያት ያለ ዕቅዱ ዴንቨር ለማረፍ ተገድዷል።
ታትሟል

ንብረትነቱ የዩናይትድ አየር መንገድ የሆነ አውሮፕላን በበረራ ላይ እያለ መንገደኛዋ መፀዳጃ ቤት ገብታ መውጣት ባለመቻሏ በረራውን አቋርጦ ለመመለስ ተገደደ።

ዕሮብ እለት ከዋሺንግተን ዲሲ ወደ ሳንፍራንሲስኮ እየበረረ የነበረው ይህ አውሮፕላን ያለ እቅዱ ዴንቨር ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማረፉን ተነግሯል።

የዩናይትን አየር መንገድ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ "የንፅህና ቤቱ በር አልሰራ አለ" ሲሉ የተፈጠረውን ተናግረዋል።

አየር መንገዱ አክሎም በመፀዳጃ ቤቱ ውስጥ ገብታ መውጣት ያልቻለችው ግለሰብ ላይ ምንም ጉዳት አለመድረሱን አስታውቋል።

በቲውተር ላይ መንገደኞች አንድ መካኒክ አልከፈት ያለውን በር ለመክፈት ሲታገል የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል አጋርተዋል።

በዚህ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ አንድ ሰው " በሩን ለመክፈት እየጣርን ነው። እንድትወጪ እናደርጋለን" ሲል ይሰማል።

ሌላ መንገደኛ በበኩሏ ለአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገረችው ሴትየዋ ታግታ ከቆየችበት መፀዳጃ ቤት ስትወጣ ደህና ትመስላለች ብላለች።

አክላም "ሴትየዋ ስትወጣ ሁላችንም በደስታ አጨበጨብን። እኛ ለእርሷ ሀዘን ገብቶን ነበር" ብላለች። በመቀጠልም "አውሮፕላኑ ሲያርፍ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ሆና ምን እንደተሰማት አላውቅም ግን ደህና ትመስላለች" ብላለች።

መንገደኛዋ በመፀዳጃ ቤቱ ውስጥ ለአንድ ሰዓት ያህል ታግታ መቆየቷ የተሰማ ሲሆን አየር መንገዱ " ሁሉንም መንገደኞች እና በመጸዳጃ ውስጥ ታግታ የቆየችውን ግለሰብ ይቅርታ እንጠይቃለን" ብሏል።