የዘንድሮው የሪዮ ካርኒቫል ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ

የብራዚል ካርኒቫል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የካቲት ወር ላይ እንዲካሄድ ታቅዶለት የነበረው የሪዮ ካርኒቫል ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የዝግጅቱ አስተባባሪዎች አስታወቁ።

የዝግጅቱ አስረባባሪ አካል የሆኑት የሳምባ ዳንስ ትምህርት ቤቶችም የኮሮናቫይረስ ክትባት ካልተገኘ በቀር ፌስቲቫሉን ማካሄድ የማይታሰብ ነው ብለው ነበር።

የሪዮ ካርኒቫል በዓለማችን ሚሊየኖች ከሚካፈሏቸው ዓመታትዊ የአደባባይ ትርኢቶች መካከል ቀዳሚ የሚባል ሲሆን ብራዚልም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ታገኝ ነበር።

ከኮሮረናቫይረስ ጋር በተያያዘ ደግሞ ብራዚል በእጅጉ ከተጠቁ የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ ስትሆን እስካሁን 4.5 ሚሊየን ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸውን አረጋግጣለች። 138 ሺህ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

'ሊዬሳ' ተብሎ የሚታወቀው የብራዚል ሳምባ ዳንሰኞች ሊግ ፕሬዝዳንት ዮርጌ ካስታንሂራ እንዳሉት የሳምባ ዳንስ ትምህርት ቤቶች ለፌስቲቫሉ ለመዘጋጀትና እስከ የካቲት ድረስ ለመቀናጀት እጅግ ከባድ ነው።

''በአሁኑ ሰዓት አማራጭ የሚሆን መፍትሄ እየፈለግን ነው። ነገሮች ወደቀደመው ቦታቸው ሲመለሱ ለከተማዋ ጥሩ የሆነ ነገር ለማበርከት እያሰብን ነው። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ቁርጥ ያለ ቀን ማስቀመጥ አልቻልንም'' ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ሊዬሳ የዘንድሮው ዓመታዊ የሪዮ ካርኒቫል ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል ይበል እንጂ በየመንገዱ የሚደረጉ አነስተኛ ዳንኪራዎች ግን ይኑሩ አይኑሩ የታወቀ ነገር የለም። ምክንያቱም የሪዮ ካርኒቫል ሲካሄድ ጎን ለጎን በሌሎች አካባቢዎች አነስተኛ ፌስቲቫሎችን ማካሄድ የተለመደ ነው።

የዘንድሮው የሪዮ ካርኒቫል ላልተወሰነ ጊዜ መራዘም ገቢያቸውና ሙሉ ሕይወታቸው በዚህ በአል ላይ የተመሰረት ብራዚላውያን ቤተሰቦችን ክፉኛ እንደሚጎዳ የሚገመት ሲሆን አገሪቱም ብትሆን በሚሊየኖች የሚቆጠር ዶላሮችን ታጣለች።

ከብራዚል አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ቱሪዝም 8 በመቶ ድርሻ አለው።