የኬንያ ባለሥልጣናትን እና ነጋዴዎችን ያስከስሳል የተባለው የሙስና ቅሌት

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
በኬንያ ለኮቪድ-19 የህክምና መሣሪያዎች የተመደበ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር መበዝበዙን ተከትሎ 15 ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ነጋዴዎች ላይ ክስ ሊመሠረት ነው።
ከፖለቲከኞች ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች እንዲሁም ነጋዴዎች ጨረታ እንዲያሸንፉ መደረጉን ምርመራው ይጠቁማል።
መንግሥት ምርመራ እንዲካሄድ የወሰነው የሕዝቡን እሮሮ ተከትሎ ነበር።
ወረርሽኙን ለመከላከል መንግሥት ከተለያዩ አካላት ወደ 2 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ድጎማ አግኝቷል።
ሆኖም ግን የጤና ባለሙያዎች ስለ መገልገያ እጥረት ቅሬታ ሲያሰሙ ነበር። ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ እንደሆነም በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
የህክምና መሣሪያዎችን የሚገዛው የኬንያ ተቋም ምንም የተሰረቀ ገንዘብ የለም ይላል።
ክሱ ምንድን ነው?
የምርመራው የመጀመሪያ ክፍል ያተኮረው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል፣ ገዋን፣ ጓንትና ሌሎችም የጤና ባለሙያዎች መገልገያዎችን ለመግዛት የተመደበው 7.8 ሚሊዮን ዶላር ያአግባብ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ ነው።
የኬንያ ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን እንዳለው፤ ጨረታ ሲካሄድ በርካታ ሕጎች መጣሳቸውን ምርመራው ይጠቁማል።
“የህክምና መሣሪያዎቹን ግዢ የመቆጣጠር ኃላፊነት በተሰጠው ተቋም የሚሠሩ ኃላፊዎች ያለአግባብ ወጪ በማውጣታቸው በወንጀል እንደሚጠየቁ ምርመራው ያሳያል” ሲል ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የኬንያ የህምና ቁሳቁሶች ገዢ ተቋም (ከምሳ) እና የጤና ሚንስትር ላይ ክስ እንዲመሠረትም ተጠይቋል።
የምርመራው ሁለተኛ ክፍል የሚያተኩረው ጨረታውን ያሸነፉ ተቋሞች ላይ ነው። በእርግጥ ተቋሞቹ ለኮቪድ-19 የተሰጠውን የድጎማ ገንዘብ ስለመበዝበዛቸው የሚጠቁም ነገር የለም።
ለሴኔት ምክር ቤት የቀረበውና ቢቢሲም የተመለከተው ሰነድ እንደሚያሳየው፤ አንዳንዶቹ ጨረታ ያሸነፉት ድርጅቶች የሳምንታት እድሜ ያላቸው ናቸው።
ለምሳሌ ሾፕ ኤንድ ባይ ሊሚትድ የተባለው ድርጅት የ10 ሚሊዮን ዶላር ጨረታ አሸንፏል። ድርጅቱ ግን የተመሠረተው ኬንያ ውስጥ የመጀመሪያ በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው ከመመዝገቡ ከሳምንታት በፊት ነው።
ድርጅቱ ምንም ስህተት አልሠራሁም ብሏል።
ሌሎቹ ጨረታ ያሸነፉ ድርጅቶች ከፖለቲከኞች ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። ከድርጅቶቹ አንዱ የኬንያዊ አገረ ገዢ ንብረት ነው።
ሰነዶች እንደሚያሳዩት፤ የኬንያ የህምና ቁሳቁሶች ገዢ ተቋም የህክምና መሣሪያዎችን ከገበያ ዋጋ በሦስት እጥፍ የገዛበት ወቅት አለ።
ተፈጽሟል የተባለው ሙስና ምን አስከተለ?
ነሐሴ ላይ የጤና ባለሙያዎች ምቹ የሥራ ሁኔታ የለም ብለው አድማ መተው ነበር።
አንዳንዶች ከደረጃ በታች የሆኑ ጓንቶችን እና ጭምብሎችን ፎቶ አንስተው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለቀዋል።
ባለሙያዎቹ አሁን ወደ ሥራ ቢመለሱም መንግሥት ቃል ገብቶ የነበረው ኮቪድ-19ን የተመለከተ የደሞዝ ጭማሪ ካላደረሳቸው በድጋሚ አድማ እንደሚመቱ አስታውቀዋል።
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፤ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የተሰጠው ድጎማ ያላግባብ ጥቅም ላይ በመዋሉ ሳቢያ ህሙማን ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በማቻኮስ ግዛት የጤና ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አንሰንት ኪቱኩ “ለኮቪድ-19 ለይቶ ማቆያ እና የጤና ባለሙያዎች የህክምና መሣሪያ የተመደበው ገንዘብ ያለአግባብ ጥቅም ላይ ውሏል። ይህም ሞት አስከትሏል” ብለዋል።
የኬንያ የህምና ቁሳቁሶች ገዢ ተቋም ሊቀ መንበር ኬምቢ ጊቱራ፤ ያለ ፍቃድ ከተመደበላቸው ዓመታዊ በጀት በላይ ማውጣታቸውን አምነዋል።
“ቦርዱ ተቋም የተመደበለትን በጀት እንዲያልፍ አልፈቀደም። ግን ያልጠበቅነው ወረርሽኝ ተከሰተ” ብለዋል።
በዚህ ወር፤ የሙስና ቅሌቱን በተመለከተ የሚያውቁትን እንዲናገሩ ምክር ቤት ለሰዓታት አፋጧቸው ነበር።
የአገሪቱ እቃ ግዢ ባለሥልጣን ጨረታ ያሸነፉትን 25 ድርጅቶች ይፋ እንዲያደርጉ ሲጠይቅ ፍቃደኛ አልሆኑም።
መንግሥት ምን እያደረገ ነው?
ፕሬዘዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የተፈጠረውን ነገር ከስር ከመሠረቱ ለማጣራት ቃል ገብተዋል።
ነሐሴ 26 ምርመራው በ21 ቀን ይጠናቀቅ የሚል ትዕዛዝ ቢያስተላልፉም ቀነ ገደቡ አልፏል።
የኬንያ ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የምርመራውን የመጀመሪያ ዙር ውጤት ለዓቃቤ ሕግ አስተላልፏል።
ኬንያ ውስጥ ከ37,000 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 659 ሞተዋል። 24,000 ደግሞ አገግመዋል። ባለፉት ሳምንታት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል።
ለጥንቃቄ ሲባል ተጥለው የነበሩ ገደቦችም እየላሉ ነው።
የሰዓት እላፊው ባይነሳም የእምነት ተቋሞች በጥንቃቄ ምዕመናንን እንዲያስተናግዱ ተፈቅዷል።
እአአ 2013 ላይ ሲመረጡ ሙስናን አስወግዳለሁ ያሉት ኬንያታ ጫና እየበረታባቸው ነው። አስተዳደራቸው በርካታ የሙስና ክሶችም ቀርበውበታል።
በምክር ቤት እየተካሄደ ያለውን ከኮሮናቫይረስ የህክምና መሣሪያዎች ጋር የተያያዘ የሙስና ክስ የሚመሩት ሴናተር ሲልቪያ ካሳንጋ፤ የኬንያ የህከምና ቁሳቁሶች ገዢ ተቋም ኃላፊዎች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ይላሉ።
“ኬንያውያን እንዲከሰሱ ይፈልጋሉ። ሁላችንም እንዲከሰሱ እንፈልጋለን። መሮናል። እጃቸው ያለበት ሰዎች ባጠቃላይ ተጠያቂ መደረግ አለባቸው” ብለዋል።












