ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩኬ የአይኤስ አባላት ናቸው የተባሉት ዜጓቿን ማስረጃ ለአሜሪካ አሳልፋ ሰጠች
ዩናይትድ ኪንግድም የአይኤስ አባላት ናቸው የተባሉት ሁለት ዜጓቸ ላይ ክስ እንዲመሰረት ለአሜሪካ ማስረጃ አሳልፋ መስጠቷ ተነገረ።
አሌክስንዳ ኮቴይ እና ኤል ሻፌ ኤልሼህ ‘ዘ ቢትልስ’ ተብሎ በሚጠራው የአይኤስ ሴል አባላት ናቸው ተብለው ተጠርጥረዋል። ሁለቱ ግለሰቦች አባል ናቸው የተባሉበት የአይኤስ ሴል የምዕራቡ አገራት ዜጎችን በማገት እና በመግደል ይወነጀላል።
አሌክስንዳ እና ኤል ሻፌ በአሁኑ ወቅት በኢራቅ በአሜሪካ ቁጥጥር ሥር ይገኛሉ። የቀረበባቸውን ክስም ተቃውመዋል። አሜሪካ ሁለቱ ሰዎች የአይኤስ አባላት መሆናቸውን እና እአአ 2014 ላይ በኢራቅ እና በሶሪያ የምዕራብ አገራት ዜጎችን አግተዋል እንዲሁም ገድለዋል ትላለች።
በሁለቱ ግለሰቦች ታግተው ተወስደው ከተገደሉት መካከል አሜሪካዊ ጋዜጠኛ እና አንድ እንግሊዛዊ የእርዳታ ድርጅት ሠራተኛ ይገኙበታል። የሁለቱ ሰዎች አንገት የአይኤስ አባላት ናቸው በተባሉ ሰዎች ሲቀላ የሚያሳየው ተንቀሳሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተሰራጭቶ ነበር።
አይኤስ በአንድ ወቅት 88ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቦታን ተቆጣጥሮ ጥብቅ የሆኑ ሕግጋቶቹን በ8 ሚሊዮን ሕዝብ ላይ ጥሎ ነበር። አሜሪካ የአይኤስ አባላት ናቸው በምትላቸው ሰዎች ላይ ክስ መስርቶ ቅጣት ለማስተላለፍ የዩኬን እርዳታ ስታገኝ ብትቆይም፤ በግለሰቦቹ ላይ የሞት ቅጣት ሊታለለፍ ይችላል መባሉን ተከትሎ ግን ዩኬ ለአሜሪካ ታደርግ የነበረውን ትብብር ገታ አድርጋው ነበር።
ባለፈው ወር አሜሪካ ሁለቱ ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ እንደማይተላለፍ ግልጽ አድርጋለች።
ዩኬ አሳልፋ የሰጠችው ማስረጃ ምንድነው?
የዩኬው የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚንስትር ፕሪቲ ፓቴል አገራቸው በሁለቱ ግለቦች ላይ የያዘችውን ማስረጃ ለአሜሪካ ማጋራቷን አረጋግጠዋል።
“አሌክስንዳ ኮቴይ እና ኤል ሻፌ ኤልሼህ ላይ ክስ እንዲመሰረት የሚያስችል ማስረጃ ለአሜሪካ ተሰጥቷል። ቤተሰቦቻቸው ለተገደሉባቸው ሰዎች ፍትህ ይሰጣል ብዬ በጽኑ አምናለሁ” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፈረዋል።
የአሜሪካ የፍትህ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ማርክ ራአሞንዲ የዬኬ መንግሥት ማስረጃዎች ተላልፈው እንዲሰጡ በመወሰኑ ደስተኞች ነን ብለዋል። የሟች ቤተሰቦቸም ሁለቱ ግለሰቦች ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ መስማታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
የአሜሪካዊው ጋዜጠኛ እህት “ሁለቱ ሰዎች ችሎት ፊት ሲቀርቡ ማየት እንፈልጋለን” ብላለች።