ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሚሊየነሩ የቻይና ፕሬዝደንት ተቺ የ18 ዓመት እስር ተበየነባቸው
የቀድሞ የመኖሪያ ቤቶች አልሚው እና የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ዢንፒንግ ተቺው በሙስና ወንጀሎች የ18 ዓመት እስር ተበየነባቸው።
የቤይጂንጉ ፍርድ ቤት ሬን ዚኪንግን “በሙስና፣ በጉቦ እና የሕዝብ ሀብት ማባከን” በሚሉ ክሶች ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
ከ18 ዓመት እስሩ በተጨማሪ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዶላር እንዲከፍሉም ተፈርዶባቸዋል።
ባለፈው ህዳር ወር ላይ ሬን አንድ አጨቃጫቂ ጽሑፍ ካሳተሙ በኋላ ደብዛቸው ጠፍቶ ቆይቶ ነበር።
ይህ ጽሑፍ ፕሬዝደንት ዢ ዢንፒንግን አጥብቆ የሚኮንን ነበር።
ሬን የቀረቡባቸው ክሶች ስለመፈጸማቸው ማመናቸውን እና በፍርዱ ላይ ይግባኝ እንደማይጠይቁ የቻይና መንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ሬን ባለሀብት ብቻም ሳይሆኑ የቀድሞ የቻይና መንግሥት ሚንስትር ልጅ ናቸው።
ከዢ ዢንፒንግ ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የቅርብ ግንኙነት አላቸው።
ሬን በፕሬዝደንቱ ላይ የሚሰነዝሩት አስተያየት በቻይናውያን ዘንድ በቀላሉ የሚታለፍ አልነበረም። የመብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ የቻይና መንግሥት ላይ ተቃውሞ የሚያስሙ ግለሰቦችን ሙስና በሚል ወንጀል ያስራል ሱሉ ይተቻሉ።
ለሬን እስር ቀጥተኛ ምክንያት ነው የተባለው ጽሑፍ ቤጂንግ የኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር የወሰደችውን እርምጃ የሚተች ነው።
የሬን ጽሑፍ ከታተመ በኋላ “በከፍተኛ የሥርዓት ጉድለት ለምርመራ ተይዘዋል” በሚል ደብዛቸው ጠፍቶ ነበር።
ከዚያም ከኮሚንስት ፓርቲው መታገዳቸው ከተሰማ በኋላ ነው የፍርድ ቤት ውሳኔው የተዘገበው።
ሬን ከቻይና መንግሥት ባለስልጣናት ጋር የሚያቃርን ጽሑፍ ሲጽፉ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ከጥቂት ዓመታት በፊት የቻይና ሕዝብ በሚከፍለው ግብር የሚተዳደሩ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን የፓርቲ ልሳን መሆናቸውን አቁመው ሕዝቡን ማገልገል ይኖርባቸዋል ብለዋል።