ኮሮናቫይረስ ፡ አሜሪካ የኮቪድ-19 ምልክት የማያሳዩ አይመረመሩም የሚለውን ውሳኔ ቀለበሰች

የኮሮናቫይረስ ምርመራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ባለፈው ወር አሜሪካ የኮቪድ-19 ምልክት የማያሳዩ ሰዎች ምርመራ ማድረግ የለባቸውም የሚል አወዛጋቢ ውሳኔ አስተላልፋ ነበር። አሁን ግን ይህ ውሳኔ በጤናው ዘርፍ አመራሮች መቀልበሱ ተገልጿል።

የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ተቋም [ሲዲሲ] እንዳለው በሽታው ካለበት ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው በአጠቃላይ መመርመር አለባቸው።

ተቋሙ ከዚህ ቀደም የነበረው አሠራር ነሐሴ ላይ ለውጥ ተደርጎበት የነበረ ቢሆንም ምርመራን በተመለከተ ወደ ቀድሞው መርህ ተመልሷል።

አወዛጋቢ የተባለው ውሳኔ የተላለፈው ያለሳይንቲስቶች ምክረ ሐሳብ ነው ተብሏል። ኒው ዮርክ ታይምስ የጠቀሳቸው ምንጭ እንዳሉት፤ ውሳኔው በሲዲሲ ድረ ገጽ መለጠፉን ባለሙያዎች ተቃውመዋል።

ሮይተርስ እንደዘገበው፤ በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች ውሳኔውን አንቀበልም ብለዋል።

ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ ያሉ እንደሚሉት በአወዛጋቢው ውሳኔ ውስጥ የፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ እጅ ሊኖርበት ይችላል። ምርመራ የሚያደርጉ ሰዎችን ቁጥር በመቀነስ ሪፖርት የሚደረጉ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን አሃዝ ለመቀነስ አስበው እንደሆነም ተጠቁሟል።

ፕሬዝዳንቱ ሰኔ ላይ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ደጋፊዎቻቸውን “ባለሥልጣኖችን እባካችሁ ምርመራ ቀንሱ ብያቸዋለሁ” ማለታቸው ይታወሳል።

አንድ የዋይት ሐውስ ባለሥልጣን የፕሬዘዳንቱ ንግግር “ቀልድ ነበር” ብለዋል።

በሌላ በኩል የሲዲሲ አመራሮች ውሳኔው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንደሌለው ገልጸዋል። ለውጡ ወቅታዊውን የኅብረተሰብ ጤናን የተመረኮዘ ነው ሲሉም ለሮይተርስ ተናግረዋል።

የቀድሞው ውሳኔ መቀልበሱ ባለሙያዎችን አስደስቷል።

የተላላፊ በሽታዎች ማኅበር ፕሬዘዳንት የሆኑት ቶማስ ፋይል "ሲዲሲ ሳይንስን መሠረት ወዳደረገ ምርመራ መመለሱ ለኅብረተሰብ ጤና መልካም ዜና ነው። ከወረርሽኙ ጋር የምናደርገውን ትግልም ያግዛል” ብለዋል።

ሲዲሲ ውሳኔውን መቀልበሱን በተመለከተ “የበሽታውን ምልክት የማያሳዩ ሰዎችን እንዲሁም በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን መመርመር ያስፈልጋል” ብሏል።

በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር በስድስት ጫማ ርቀት ቢያንስ ለ15 ደቂቃ የተገናኙ ሰዎች የበሽታውን ምልክት ባያሳዩም እንዲመረመሩ ተቋሙ ይመክራል።

በአሜሪካ በአሁኑ ወቅት ወደ 7 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። ይህም በመላው ዓለም በሽታው ከተገኘባቸው የሰዎች ብዛት አንድ አምስተኛው ነው። በወረርሽኙ ሳቢያም 200,000 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፤ ይህም ከዓለም አገራት ከፍተኛው ነው።