ሊቢያ፡ የካሊፋ ሀፍታር አስተዳደር የቤንጋዚ ተቃውሞን ተከትሎ ሥራ ለቀቀ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የምሥራቅ ሊቢያው ተቀናቃኝ መንግሥት ሕዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ሥራ ሊለቅ ነው።
ተቃውሞ የተቀሰቀሰው የኑሮ መላሸቅና የሙስና መንሰራፋትን ተከትሎ ሲሆን፤ ሰልፈኞች ቤንጋዚ ውስጥ የጄነራል ካሊፋ ሀፍታር ዋና መሥሪያ ቤት አካባቢን አጋይተዋል።
ከጄነራል ሀፍታር ይዞታዎች አንዱ በሆነው አል-ማጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ግጭት ተቀስቅሷል።
ጋዳፊ በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ኃይሎች ከተገደሉ በኋላ ሊቢያ ሰላም ርቋታል።
የጄነራል ሀፍታር ቃል አቀባይ እንዳሉት፤ አስተዳደራቸው ሰላማዊ ተቃውሞን ቢደግፍም፤ “በሽብርተኞችና በሙስሊም ወንድድማችነት አባላት እንዲጠለፍ አንፈቅድም” ብለዋል።
እስካሁን ድረስ የሊቢያ ተቃውሞ በመዲናዋ ትሪፖሊ የተወሰነ ነበር። ትሪፖሊ ያለው መንግሥት በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተሰጠው ነው።
የጀነራል ሀፍታር ኃይል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2019 ላይ ትሪፖሊን ለመያዝ ሞክሮ እንደነበር ይታወሳል። ሆኖም ግን በቱርክ የሚደገፈው የመንግሥት ኃይል በሩስያ የሚደገፈውን የሀፍታር ኃይል አስወጥቷል።
ባለፈው ወር በሊቢያ ተቀናቃኝ መንግሥቶች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።
ግንቦት ላይ ሾልኮ የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ ሊቢያ ውስጥ ‘ዋግነር ግሩፕ’ በተባለ ተቋም ስር ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቅጥረኛ ወታደሮች እየተንቀሳቀሱ ነው። የተቋሙ መሪ የቭጀንሲ ፒጎዚህ ከሩስያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ይቀራረባሉ።
ጄነራል ሀፍታር በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በግብፅ ሲደገፍ ትሪፖሊ የሚገኘው መንግሥት ደግሞ በቱርክ፣ ካታር እና ጣልያን ድጋፍ ይሰጠዋል።
ባለፉት ወራት የጄነራል ሀፍታር ደጋፊዎች ወደ ነዳጅ ማውጫ የሚያስኬዱ መንገዶችን ዘግተዋል። ይህም የኃይል መቆራረጥ አስከትሏል። ሊቢያን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላርም አሳጥቷታል።
ባለፈው ወር ግን በነዳጅ ማቆያ ውስጥ ያለ ነዳጅ እንዲሸጥ ቢፈቀድም፤ አዲስ ምርት ላይ ክልከላ ተጥሏል።














