እግር ኳስ፡ የአፍሪካ ዋንጫ ካይሮ ውስጥ ጠፋ

ታትሟል

የአፍሪካ ዋንጫን ጨምሮ በርካታ ዋንጫዎች ካይሮ ከሚገኘው ከግብጽ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና መስሪያ ቤት መጥፋታቸው ተነገረ።

የግብጽ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በጉዳዩ ላይ ይፋዊ ምርመራ ጀምሪያለሁ ብሏል።

ግብጽ እአአ 2010 ተከታታይ ሶስተኛ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ መሆኗን ተከትሎ ነበር ዋንጫው ግብጽ እንድትወስደው የተደረገው።

ግብጽ የአፍሪካ ዋንጫን ለተከታታይ ሶስት ጊዜ ያሸነፈችው በ2006፣ 2008 እና 2010 በተደረጉት ውድድሮች ነበር።

አርብ ዕለት የግብጽ እግር ኳን ፌደሬሽን በርካታ ዋንጫዎች መጥፋታቸውን ተከትሎ ይፋዊ ምረመራ መጀመሩን አስታውቋል።

''ፌደሬሽኑ ዋና መስሪይ ቤቱን በማደስና ወደ ሙዚየምነት ለመቀየር እየተሯሯጠ ባለበት ወቅት የዋንጫዎቹ መጥፋት አመራሩን በጣም አስደንግጦታል'' ብሏል ፌደሬሽኑ ባወጣው መግለጫ።

የቀድሞው የግብጽ እግር ኳስ ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አህመድ ሾቢር በበኩላቸው ከጠፉት ዋንጫዎች መካከል የ2010ሩ ዋንጫም እንደሚገኝበት ተናግረዋል።

በአውሮፓውያኑ 2013 የግብጽ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና መስሪያ ቤት ጥቃት ከተፈጸመበት በኋላ ዋንጫዎቹ ወደ ሌላ ማቆያ ስፍራ እንዲወሰዱ ተደርጎ ነበር።

ነገር ግን የፌደሬሽኑ ባለስልጣናት የመስሪያ ቤቱን መግቢያና መውጫ በሮች በማስተካከል ጎብኚዎች ዋንጫዎቹን እንዲጎበኙ ለማድረግ እድሳት በሚሰሩበት ወቅት ነው ዋንጫዎቹ መጥፋታቸውን ይተነገረው።

በአፍሪካ አግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ወይንም ካፍ ሕግ መሰረት አንዲት አገር ዋንጫውን ለሶስት ተከታታይ ጊዜ ካሸነፈች ዋንጫውን ማስቀረት ትችላለች። በዚህም ሕግ መሰረት ነው ግብጽ ዋንጫውን በአገሯ ያስቀረችው።

በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ለሶስት ተከታታይ ጊዜ ማሸነፍ የቻለችው ሌላኛዋ አገር ጋና ስትሆን ሶስተኛውን ዋንጫ ያነሳችው በአውሮፓውያኑ 1978 ላይ ነበር።