ኢስላሚክ ስቴት፡ በርካታ የአይኤስ ፕሮፓጋንዳ ጽሑፎች በድረ ገጽ ቤተ መጻሕፍት ተገኙ

ታትሟል

ኢንስቲትዩት ኦፍ ስትራቴጂክ ዳያሎግ በተሰኘ የድረ ገጽ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ በርካታ የኢስላሚክ ስቴት የፕሮፓጋንዳ ጽሑፎች መገኘታቸው ተገለጸ።

ቤተ መጻሕፍቱ ወደ 90 ሺህ ጽሑፎች ያሰባሰበ ሲሆን፤ በየወሩ 10 ሺህ ገደማ ጎብኚዎች አሉት።

ተንታኞች እንደሚሉት፤ አክራሪነትን የሚያበረታተቱ ጽሑፎች በድረ ገጹ ይገኛሉ። ሆኖም ግን የጽሑፍ መረጃዎቹ አንድ ቦታ ስለማይከማቹ ለማስወገድ አስቸጋሪ ነው።

በብሪትን እና በአሜሪካ ያሉ የጸረ ሽብር ኃይሎች ስለ መረጃ መረቡ ቢያውቁም፤ ገጹ እያደገ መጥቷል።

ጽሑፎቹ የተገኙት የአይኤሱ መሪ አቡበከር አልባግዳዲ አምና ከተገደለ በኋላ ነው። በወቅቱ ቡድኑን ከሚደግፉ የማኅበራዊ ሚዲያ ጽሑፎች ጋር አጭር ማስፈንጠሪያ ተያይዞ እየተሰራጨ ነበር።

ማስፈንጠሪያው በዘጠኝ ቋንቋዎች ወደተጻፉ ሰነዶችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ይወስዳል። ይህም እአአ 2017 ላይ በማንችስተር ስለደረሰው ጥቃት፣ እአአ 2015 ላይ በለንደን ስለደረሰውን ጥቃት እና እአአ 2001 ላይ በአሜሪካ ስለደረሰው ጥቃት ዝርዝር መረጃ ይሰጣል።

የቤተ መጻሕፍቱ ዳይሬክተር ሙስጠፋ አያድ፤ ጥቃት ስለመሰንዘር የሚገልጹ ጽሑፎች እንዳሉ ተናግሯል።

አጥኚዎች ባለፉት ወራት ተቋሙ እንዴት እንደሚንቀሳቀስና ማን እንደሚጎበኘው በቅርበት ሲከታተሉ ነበር።

መረጃ የሚቀመጠው በአንድ ኮምፒውተር ሳይሆን ባልተማከለ ሥርዓት ተሰራጭቶ ነው። ማንም ሰው ጽሑፎቹን ማጋራት ይችላል። ድረ ገጹን ማውረድ የሚከብደውም ለዚህ ነው።

ጽሑፎቹ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች በሐሰተኛ አካውንት ይሰራጫሉ። የታዋቂ ሰዎችን የትዊተር ገጽ መመዝበርም ሌላው መንገድ ነው።

ከዚህ ቀደም አይኤስ የጀስቲን ቢበርን ገጽ ሰብሮ በመግባት መረጃ ማሰራጨቱ ይታወሳል።

ድረ ገጹ ላይ ስለ አይኤስ ሐሳብ፣ ስለ ሃይማኖትና ሌሎችም የፕሮፓጋንዳ ጽሑፎች ይገኛሉ። ከቤታቸው ጠፍተው አይኤስን ስለተቀላቀሉ ወጣቶች አኗኗርም መረጃ አለ።

ቡድኑን ከሚቀላቀሉ አብዛኞቹ ከ18 እስከ 24 እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ የአረቡ ዓለም ወንዶች ናቸው። 40 በመቶ የሚሆኑት የሚገኙት ከዩቲውብና ሌሎችም ማኅበራዊ ሚዲያዎች ነው።

ሌሎች ጽንፈኛ ቡድኖችም ተመሳሳይ መንገድ ይከተላሉ።

በጂሀድ ጉዳዮች ላይ የምትጽፈው የቢቢሲዋ ሚና አልላሚ “ጽሑፎቹ ባልተማከለ ሁኔታ ስለሚከማቹ በአንድ ሰርቨር አይገኙም። በተለያዩ ተጠቃሚዎች ኔትወርክ ተከፋፍሎ ይገኛል። ይህም ጂሀዲስቶችን ይስባል” ትላለች።

ጽሑፎቹን ያገኟቸው ተመራማሪዎች ጉዳዩን ለአሜሪካ ዓቃቤ ሕግ የጸረ ሽብር ክፍል አስታውቀዋል።