ኮሮናቫይረስ፡ የቀድሞው የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር በርሎስኮኒ ሆስፒታል ገቡ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የጣልያን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ በርሎስኮኒ 83 ዓመታቸው ሲሆን በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ሚላን በሚገኝ ሆስፒታል ገብተው እንደነበር ተገለፀ።
የቤርሎስኮኒ ፓርቲ፣ ፎርዛ፣ የጤንነታቸው ሁናቴ የሚያሰጋ አለመሆኑን በመግለጽ "ደህና ናቸው" ብሏል።
ቤርሎስኮኒ ከሁለት ልጆቻቸው ጋር በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠው በሳርዲና ከተማ የእረፍት ጊዜቸውን ካሳለፉ በኋላ ነው።
ሳርዲና ከጣሊያን ከተሞች ሁሉ ከፍተኛ የኮሮናቫይረስ ስርጭት የሚታይባት ከተማ ናት።
ሐሙስ እለት በሚላን አቅራብያ እንዲቆዩ መደረጉ ተገልጿል።
" የኮቪድ-19 ሁኔታቸውን ለመከታተል አነስተኛ የጥንቃቄ እርምጃ አስፈላጊ በመሆኑ እንጂ ደህና ናቸው" ያሉት የፎርዛ ኢጣልያ ሴናተር ሊቺያ ሮንዙሊ ናቸው።
ሐሙስ ምሽት በርሎስኮኒ በሰሜን ሚላን ከሚገኘው ቤታቸው ወደሳን ራፋዔል ሆስፒታል ተወስደው ለይቶ ማቆያ ክፍል እንዲገቡ ተደርገዋል።
ቀደም ብሎ የግል ሐኪማቸው፣ አልቤርቶ ዛንግሪሎ፣ በርሎስኮኒ ምልክት የማይታይባቸው መሆኑን ገልፀው ነበር።
የጣልያን መገናኛ ብዙኃን የበርሎስኮኒ አጋር የሆነችው የ30 ኣመቷ ወጣት ማርታ ፋስቺናም በኮቪድ-19 መያዟ በምርመራ መረጋገጡን ዘግበዋል። ወይዘሪት ፋስቺና ፎርዛ ኢታሊያን በመወከል የምክር ቤት አባል ስትሆን ከፍቅር አጋሯ ሲልቪያ በርሎስኮኒ ጋር በለይቶ ማቆያ ትገኛለች።
በርሎስኮኒ ለፓርቲያቸው አክቲቪስቶች ሐሙስ ዕለት በስልካቸው ባስተላለፉት መልዕክት " በቻልኩት ሁሉ በቀጣዩ ምርጫ ላይ እሰራለሁ" ካሉ በኋላ በቫይረሱ እንዴት ሊያዙ እንደቻሉ እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ጣልያን ከዚህ ቀደም ለማካሄድ ቀጠሮ ይዛለት የነበረውና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ ወደ መስከረም ወር መጨረሻ አካባቢ የተገፋውን ክልላዊ ምርጫ ታካሄዳለች።















