ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕንድና ቻይና፡ ሁለቱን የኒውክሌር ባለቤት ሃገራት ምን አጣላቸው?
ሕንድ፤ ቻይና በቅርቡ ሁለቱ ሃገራት የገቡትን የሰላም ስምምነት ጥሳ 'ድንበሬን እየተጋፋች' ነው ስትል ወቀሰች።
ሕንድ እንደምትለው በሁለቱ ሃገራት ድንበር ላይ የምትገኘው ላዳክ አካባቢ ያሉ የቻይና ጦር ሠራዊት አባላት ግጭት ቀስቃሽ እንቅስቃሴ አድርገዋል።
ባለፈው ሰኔ በሁለቱ ሃገራት ድንበር ላይ በተነሳ ግጭት 20 የሕንድ ወታደሮች መሞታቸው አይዘነጋም። ቻይና ግን በወቅቱ በተነሳው ግጭት ያጣችው ወታደር ስለመኖሩ ያለችው ነገር የለም።
የኒውክሌር ጦር ባለቤት የሆኑት ሁለቱ የአህጉረ እስያ ኃያላን ሃገራት፤ ድንበር ላይ ለሚከሰት ግጭት እስር በርስ ይወቃቀሳሉ።
ቻይና ወታደሮቼ የተደረሰውን ስምምነት አልጣሱም ስትል ወቀሳውን ታስተባብላለች።
"ድንበር የሚጠብቁ የቻይና ጦር ሰራዊት አባላት ምንም ጊዜም ሕግ ያከብራሉ። ድንበር ተሻግረውም አያውቁም። የሁለቱ ሃገራት ወታደሮች በድንበር ጉዳይ ውይይት ያደርጋሉ" ብለዋል የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዣዎ ሊጂያን።
ሕንድ ግን 'ወታደሮቼ ቅዳሜ ምሽት የቻይና ወታደሮችን እንቅስቃሴን መክተዋል' ትላለች።
የሕንድ መንግሥት ባወጣው መግለጫ "የቻይና ወታደሮች እውነታን ለመቀየር ያደረጉትን ሙከራ ለመመከት አስፈላጊውን እርምጃ ወስደናል" ይላል።
አክሎም "ሕንድ የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ተግባራዊ ናት፤ የዚያኑ ያክል ድንበሯን ለመጠበቅ ቁርጠኛ ናት" ይላል መግለጫው።
ተንታኞች የሕንድ መግለጫ ድንበር አካባቢ ተግባራዊ እንዲሆን የተደረሰው ስምምነት መጣሱን ያሳያል ይላሉ።
ሰኔ ላይ ምን ተፈጠረ?
የመገናኛ ብዙሃን የሁለቱ ሃገራት ወታደሮች 4300 ሜትር ርዝማኔ ያለው ተራራ ላይ መጋጨታቸውንና እና የተወሰኑ የሕንድ ወታደሮች ጋልዋን ወደተሰኘ ወንዝ ወድቀው መሞታቸውን ዘግበው ነበር።
በወቅቱ ቢያንስ 76 የሕንድ ወታደሮች መጎዳታቸውና 20 ደግሞ መሞታቸው ተነግሮ ነበር።
ቻይና በግጭቱ የሞተም ሆነ የተጎዳ ወታደር ስለመኖሩ ምንም ዓይነት መረጃ አልሰጠችም።
ወታደሮቹ ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያ እንዳልተጠቀሙም ተነግሮ ነበር። ይህ የሆነው ደግሞ ሁለቱ ሃገራት በ1989 በገቡት ስምምነት መሠረት ድንበር አካባቢ የጦር መሣሪያ መጠቀም ስለማይቻል ነው።
ከዚህ ግጭት በኋላ ቻይናና ሕንድ በርካታ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያው ውይይቶችን አካሂደው ጉዳዩን ለመፍታት ሞክረዋል። ነገር ግን ሁለቱም ሃገራት በድንበር አካባቢ እየተካሄደ ስላለ ግንባታ እርስ በርስ ሲወቃቀሱ ይሰማሉ።
ተንታኞች ድንበሩ ከሰኔ ጀምሮ ሰላም እንደራቀው ይናገራሉ።
ዘ ላይን ኦፍ አክቹዋል ኮንትሮል በመባል የሚታወቀው የሁለቱ ሃገራት ድንበር በውል ባለመከለሉ ምክንያት ግጭት ያጭራል። አካባቢው በወንዞችና ሐይቆች የተሞላ መሆኑ የድንበሩ መስመሩ እንዲዋዥቅ ምክንያት ሆኗል።
ከዓለማችን በርካታ ወታደሮች ካሏቸው ሃገራት መካከል ዋነኛ የሆኑት ሕንድና ቻይና በፈረንጆቹ 1962 ጦርነት ገጥመው ሕንድ መሸነፏ አይዘነጋም።
ሕንድ፤ ቻይና 38 ሺህ ስኩዌር ኪሎሜትር መሬት ነጥቃኛለች ስትል ትከሳለች።
ምንም እንኳ ሁለቱ ሃገራት በድንበር ይጣሉ እንጂ ጥሉ ኃያልነትን የማሳየት ጉዳይ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።
ሕንድ በቅርቡ ወደ ላዳክ የሚወስድ መንገድ መገንባቷ ወደ ሥፍራው ወታደርና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ለማጓጓዝ ይረዳታል፤ ይህ ደግሞ ቻይናን ሳይስቆጣ አልቀረም ይላሉ ተንታኞች።