ኮሮናቫይረስ፡ ደቡብ ኮርያ የኮቪድ-19 ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ሕጓን አጠበቀች

ታትሟል

በደቡብ ኮርያ ዋና ከተማ የኮቪድ-19 ስርጭት መስፋፋቱን ተከትሎ ሙዚየሞች፣ የምሽት ጭፈራ ቤቶች፣ እንዲሁም መጠጥ ቤቶች ተዘግተዋል።

ማክሰኞ ዕለት የቫይረሱ ስርጭት ለአምስተኛ ቀን ወደ ሶስት ዲጂት ከፍ ያለ ሲሆን በአብዛኛው እድሜያቸው በ40ዎቹ ውስጥ የሆኑ ሰዎች መጠቃታቸው ታውቋል።

ደቡብ ኮርያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን በፍጥነት በመቆጣጠር ስሟ በተደጋጋሚ ሲነሳ ነበር። ነገር ግን ከቤተ እምነቶች ጋር በተያያዘ የተቀሰቀሰው ዳግም ወረርሽኝ ስጋትን አጭሯል።

ደቡብ ኮርያ ማክሰኞ ዕለት 246 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን በምርመራ ስታረጋግጥ በአገሪቷ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 15,761 ደርሷል።

አብዛኛዎቹ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው ግለሰቦች በሳራንግ ዤይል ቤተ ክርስትያን ጋር የሚገናኙ ሲሆን፣ የቤተ እምነቷ ፓስተር የፕሬዝዳንት ሙን ዤ-ኢን ቀንደኛ አብጠልጣይ ናቸው።

ይህ በደቡብ ኮርያ የተከሰተው አዲስ ወረርሽኝ በሌላ እምነት ስፍራም ይዛመታል የሚል ፍራቻ ቀስቅሷል። በደቡብ ኮርያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱ ሲታወቅ መነሻው የነበረው ሺንቼዮንጂ ቸርች ኦፍ ጂሰስ ነበር።

ከዚህ ቤተ እምነት ጋር ግንኙነት ያላቸው 5,200 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው መገኘታቸው ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ 457 ከሳራንግ ዤይል ቤተክርስትያን ጋር ይያያዛል ተብሏል።

ከእነዚህ መካከል አስር ግለሰቦች ባለፉት ሁለት ሳምንታት በዋና ከተማዋ ሶል በተደረገ መንግሥትን በሚቃወም ሰልፍ ላይ ተሳትፈው እንደነበር ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የደቡብ ኮርያ ባለሥልጣታናት ማንኛውም ቤተ እምነት የአምልኮ ስርዓቱን በቤተ እምነቶች ውስጥ እንዳያካሂድ ያገዱ ሲሆን የቫይረሱ ስርጭት ታይቶባቸዋል የተባሉ ቤተ እምነቶችን ምዕመናን፣ ራሳቸውን ለይተው እንዲቀመጡ እና ምርመራ እንዲያደርጉ የመለየት ስራ እየሰሩ ነው።

"አሁን ያለው ስርጭትን መቆጣጠር ካልቻልን ቀውስ ውስጥ እየገባን ነው፣ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ያደርጋል፣ ይህ ደግሞ ህክምና ስርዓታችን እንዲንኮታኮትና ከፍተኛ የሆነ የምጣኔ ሃብት ድቀት እንዲደርስ ያደርጋል" ብለዋል የኮሪያ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ድርጅት ዳይሬክተር ዢዮንግ ኢኡን ኬኦንግ።

ከዛሬ ረብዑ ጀምሮም 12 ለአደጋ ተጋላጭ የተባሉ የንግድ ዘርፎች በዋና ከተማዋ ሶል፣ ኢንቺዮን እና በተጎራባች የጊዮንጊ ግዛት እንዲዘጉ ተወስኗል፤ ከእነዚህም መካከል ፣ የምሽት ጭፈራ ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች፣ አገልግሎት መስጠት እንዲያቆሙ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

ሙዚየሞችም የተዘጉ ሲሆን በቤት ውስጥ ከ50 ሰው በላይ፣ ከቤት ውጪ ደግሞ ከ100 ሰው በላይ ሆኖ መሰብሰብ ታግዷል።