ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሕንድ በኮቪድ-19 ፅኑ ህሙማን ክፍል በተነሳ እሳት ስምንት ሰዎች ሞቱ
በሕንድ ምዕራባዊ ከተማ አህሜዳባድ በሚገኝ የኮቪድ -19 ሆስፒታል ከፅኑ ህሙማን ክፍል በተነሳ እሳት ሳቢያ የስምንት ህሙማን ሕይወት ማለፉ ተገለፀ።
የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ራጀሽ ብሃት ለቢቢሲ እንደተናገሩት እሳቱ የተነሳው አንድ የሆስፒታሉ ሰራተኛ የበሽታ መከላከያ መሳሪያ ባጋጠመ የኤሌክትሪክ ችግር ሳቢያ በእሳት በመያያዙ ነው ብለዋል።
ሰራተኛዋ በድንጋጤ ወደ ፅኑ ሕሙማን ክፍል የገባች ሲሆን እሳቱም በዚያ መዛመቱን የገለፁት ባለሙያው፤ ይህንንም ተከትሎ አንድ የሆስፒታሉ ዳሬክተር በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ መጀመሩን አስረድተዋል።
ባለሙያው አክለውም ምሽት 3፡30 ገደማ የተነሳው የእሳት አደጋው ከአንድ ሰዓት በኋላ በቁጥጥር ሥር መዋሉን እና በዚያው የሚገኙ 40 ህሙማንም ወደ ሌላ ክፍል መዛወራቸውን ገልፀዋል።
ይህንን ተከትሎም እርሳቸውና የእሳትና ድንገተኛ ክፍል ቡድን ከህሙማኑ ጋር የቅርብ ንክክኪ ስለነበራቸው ወደ ለይቶ ማቆያ እንደሚገቡ ተናግረዋል።
ዋና ከተማዋ አህሜዳባድ የሆነችው ጉጃራት ግዛት ሚኒስተር ሆነው ያገለገሉትና ጠቅላይ ሚኒስተር ናሬዳንድራ፤ በተፈጠረው አደጋ ማዘናቸውን ገልፀው ለተጎጂ ቤተሰቦች የመቋቋሚያ ድጋፍ እንደሚደረግ በትዊትር ገፃቸው አስፍረዋል።
አሁን በሥራ ላይ ያሉት የግዛቷ ሚኒስተር ቪጃይ ሩፓኒ በበኩላቸው ሃዘናቸውን ገልፀው በአደጋው ላይ ምርምራ እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተወሰኑት ተጎጂዎች ቤተሰቦች "ሆስፒታሉ እሳት አደጋ ክፍል ለመጥራት ዘግይቶ ነበር" በማለት አንዳንድ የተጎጂ ቤተሰቦች ስለ አደጋው እንዳልተነገራቸው ይከሳሉ።
" የሆስፒታሉ ሰራተኞች ምንም ዓይነት መረጃ አልሰጡንም። ማንም እሳቱ እንዴት ሊነሳ እንደቻለ እና ምን እንደተፈጠረ የነገረን የለም" ሲሉ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ የነበረውን ሁኔታ ተናግረዋል።
ፖሊስ ለአደጋው ተጠያቂ የሆነውን አካል ለመለየት ሦስት ቀናት የሰጠ ሲሆን፤ አደጋውን አንደ ድንገተኛ አደጋ በመመዝገብ አንድ የሆስፒታሉን ዳይሬክተር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።