በህንድ በመጠጥ መመረዝ የበርካቶች ህይወት አለፈ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በህንድ በመጠጥ መመረዝ የ86 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገልጿል።
ግለሰቦቹ በህገወጥ መንገድ የተመረተ አልኮል በመጠጣታቸው ህይወታቸው ማለፉን የሰሜን ህንዷ ግዛት ፑንጃብ ኃላፊዎች አስረድተዋል።
በትናንትናው ዕለት ፖሊስ አካባቢውን በመቆጣጠር ህገወጥ የተባለውን መጠጥ የያዘ ሲሆን መጠጡን ያመርታሉ የተባሉ 25 ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
የሟቾችም ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው ተብሏል።
በህንድ በመጠጥ መመረዝ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሲሞቱ አዲስ አይደለም፤ በተደጋጋሚም የሚከሰት ችግር ነው ተብሏል።
በየአመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህንዳውያን በጓዳ ጎድጓዳው ንፅህናው ባልተጠበቀ መልኩ የሚጠመቁ መጠጦችን በመጠጣት ህይወታቸው ያልፋል።
በተለይም በገጠሯ ህንድ ታዋቂ ስም ያላቸውን መጠጦች ከመግዛት ይልቅ በህገ ወጥ መንገድ የተመረቱና ዋጋቸው ርካሽ የሆኑ መጠጦችን ይገዛሉ፤ በዚህም በርካቶች መመረዛቸው ሪፖርት ይደረጋል።
መጠጥ ጠማቂዎች ሜታኖል የሚባለው ንጥረ ነገር ይጨምሩበታል። ይህ ንጥረ- ነገር ከፍተኛ መርዛማነት ያለው ሲሆን የመጠጡን ጥንካሬም ለመጨመርም ነው ሜታኖልን የሚጨምሩበት ተብሏል።
በትንሽም መጠን ቢሆን ይህ ንጥረ ነገር ከተወሰደ አይነ ስውርነት፣ የጉበት ህመም እንዲሁም ባስ ሲል ሞት እንደሚያስከትልም ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በዚህ ሳምንት አርብም የፑንጃብ ግዛት አስተዳዳሪ ሚኒስትር አማሪንደር ሲንግ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ላይ ምርመራ እንዲጀመር አዘዋል።
በርካታ ሪፖርቶች እንደሚያስረዱት መጠጡ በከፍተኛ መጠን እንደተጠመቀና ጎዳናዎች ላይ ላሉ የካፌ ባለቤቶች እንደተሸጠና የአካባቢው ማህበረሰብም መጠጡን ማግኘቱ ተገልጿል።
ከሰሞኑም በሕንድ ውስጥ በምትገኘው አንድራ ፕራዴሽ ግዛት የመጠጥ መሸጫ ሱቆች መዘጋታቸውን ተከትሎ በርከት ባለ አልኮል የተሰራ ሳኒታይዘር የጠጡ ቢያንስ አስር ግለሰቦች ሕይወታቸው ማለፉ ተዘግቧል።
የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ እንደተናገሩት ሰዎቹ ሕይወታቸው ሊያልፍ የቻለው ሳኒታይዘሩን ከውሃ እና ከለስላሳ መጠጦች ጋር ቀላቅለው በመጠጣታቸው ነው።












