ሕንድ፡ ሳኒታይዘር የጠጡ ቢያንስ 10 ሰዎች ህይወታቸው አለፈ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በሕንድ ውስጥ በምትገኘው አንድራ ፕራዴሽ ግዛት የመጠጥ መሸጫ ሱቆች መዘጋታቸውን ተከትሎ በርከት ባለ አልኮል የተሰራ ሳኒታይዘር የጠጡ ቢያንስ አስር ግለሰቦች ሕይወታቸው ማለፉ ተዘገበ።
የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ ሲዳርት ኩሻል እንደተናገሩት ሰዎቹ ሕይወታቸው ሊያልፍ የቻለው ሳኒታይዘሩን ከውሃ እና ከለስላስ መጠጦች ጋር ቀላቅለው በመጠጣታቸው ነው።
አክለውም ''ሁሉም አልኮል ላይ ጥገኛ ነበሩ" ያሉት የፖሊስ ኃላፊው፤ የሳኒታይዘር፣ ውሃ እና ለስላስ መጠጦች ቅልቅሉን መጠጣት የጀመሩት ከመሞታቸው አስር ቀናት በፊት እንደሆነ ተናግረዋል።
''ሳኒታይዘሩ ለጤና ጎጂ የሆነ መርዛማ ንጥረነገር በውስጡ ስለመኖሩና አለመኖሩ ምርመራ እያካሄድን እንገኛለን'' ካሉ በኋላ ከሳኒታይዘሩ የተወሰዱ ናሙናዎች ለኬሚካል ምርመራ መላካቸውን አስታውቀዋል።
አንዳንድ በከፍተኛ ሁኔታ የአልኮል ሱሰኛ የሆኑ ሰዎች አልኮል ማግኘት ሳይችሉ ሲቀሩ የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘሮችን እንደ አማራጭ እየተጠቀሙ እንደሆነ ኃላፊው ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገልጸዋል።
ኩሪቼዱ በተባለችው መንደር በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ማሻቀቡን ተከትሎ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል።
''በእንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት አልኮል አይሸጥም፤ ነገር ግን ሳኒታይዘሮቹ በቀላሉ መገኘት የሚችሉ ናቸው'' ብለዋል።
የሕንድ ፌደራል መንግሥት ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት በማሰብ አንዳንድ የንግድ ተቋማት መልሰው እንዲከፈቱ መወሰኑ የሚታወስ ነው። በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይም እንደ ዮጋ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያዎች እንዲከፈቱና የሰዎች እንቂስቃሴ እንዲጀመር ተደርጓል።
ነገር ግን በርካታ የአገሪቱ ግዛቶች ቫይረሱ እየጨመረ በመጣባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የእንቅስቃሴ ገደቦችን አስቀምጠዋል።
በደቡባዊ ሕንድ በምትገኘው አንድራ ፕራዴሽ ግዛት ባለፈው ወር ብቻ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ መጨመሩን የግዛቲቱ መንግሥት አስታውቆ ነበር።
ሕንድ ውስጥ በየቀኑ እስካሁን ከ55 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ ሲሆን በአጠቃላይ በቫይረሱ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ37 ሺ በላይ ደርሷል።
















